Search

አፈርን ወደ ማዕድንነት የሚቀይሩት ኮንታዎች

ቅዳሜ ታኅሣሥ 04, 2018 112

ኮንታ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ይገኛል። አካባቢው ያልተገለጠ እምቅ ሀብት ባለቤት ነው።

የመደመር መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አማካይነት የገለጠው የዝሆን ዳና ሎጅ ቱሪስቶችን እያስተናደ ይገኛል።

የኮንታ ሕዝብ የሚታወቅበት ሌላው ሀብቱ የችግር መፍቻ የሆነው ሀገር በቀል ዕውቀቱ ነው። በኮንታ አባቶች ለትውልድ ያስተላለፉት ዕውቀት ዛሬም ይተገበራል።

አፈርን ወደ ብረት ማዕድንነት የመቀየር ጥበብ በኮንታ ዞን፣ ኦሽካ ዴንቻ አካባቢ ነዋሪዎች ዘንድ በቀላሉ ይከወናል።

በኮንታዎች ዘንድ መሬት ውስጥ የብረት ማዕድን መኖር አለመኖሩን ለማወቅ በመጀመሪያ መሬቱ በእግር መታ መታ ይደረጋል፤ ከዚያም ጆሮን መሬት ላይ ለጥፎ በማድመጥ ማዕድን መኖር አለመኖሩ ይለያል።

ማዕድን መኖሩ ከታመነ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ይመርቁና ወንዶች የማዕድን ይዘት ያለው አፈር ቆፍረው ያወጣሉ።

በሴቶቹ በኩል ትልልቅ መቀቀያ ጋኖች ይዘጋጁና አፈሩን ወደ ጋኑ በመጨመር በዙሪያው ያለማቋረጥ እሳት በወናፍ በማንደድ አፈሩ ቀልጦ እስኪፈስ ድረስ ይቀቀላል።

በዚህ መሀል ታዲያ የሚበላና የሚጠጣው ተዘጋጅቶ የሚሠሩ ሰዎች በባህላዊ ሙዚቃ ጭምር እንዲነቃቁ እና እንዲበረቱ ይደረጋል።

በደንብ ከቀለጠ እና ከአፈሩ ከተለየ በኋላ በኋላ ብረት ማዕድኑ ላይ ውሃ ጨምሮ በማቀዝቀዝ በእርሻ መሣሪያ፣ የቤት ውስጥ መገልገያ እና ጌጣጌጥ መልክ ተበጅቶ ለሽያጭ ይቀርባል።

በአካባቢው 4 ሺህ ሄክታር ቦታ ላይ የብረት ማዕድን ስለመኖሩ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አበበ ደምሴ ይገልፃሉ።

ይህ ሀብት ጥልቅ ጥናት ተካሂዶበት የአካባቢውን ነዋሪ በስፋት ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን የሚያነሱት ኃላፊው፤ አልሚ ባለሀብቶች ቢሳተፉበት የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል ባይ ናቸው።

እስከአሁን የሚሠራበት ባህላዊው የማዕድን ማውጣት ጥበብ በቴክኖሎጂ ቢታገዝ የመደመር መንግሥት ለማዕድን ሀብት ለሰጠው ትኩረት አጋዥ ሚና እንደሚኖረው እሙን ነው።

በሲሳይ ደበበ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #bloomery #traditionalfurnace #ironsmelting