Search

የጌዲኦ ማህበረሰብን ከግጭት በማውጣት ወደ እርቅና ሰላም ጎዳና የመራው ባህላዊ ሽምግልና

እሑድ ታኅሣሥ 05, 2018 105

በ2009 ዓ.ም በጌዲኦ ዞን ተከስቶ የነበረው ግጭት ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት አስከትሏል።

በወቅቱ ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ የዞኑ የሀገር ሽማግሌዎች የወሰዱት እርምጃ ጉዳቱ ከዚያ በላይ እንዳይከፋ አስችሏል።

የሀገር ሽማግሌዎቹ ተግባር በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ሲከሰቱ የመፍቻ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ውጤታማ ተሞክሮ ሆኗል።

40 የሚሆኑ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ ተሰባስበው በዞኑ ሰላምን ለማረጋገጥ ያከናወኑት ሥራ የጌዲኦ ማህበረሰብን ከግጭት በማውጣት ወደ እርቅና ሰላም ጎዳና መርቷል።

በወቅቱ ይህ የጌዲኦ ባህላዊ ሽምግልና የተመራው በሁለት መሠረታዊ መርሆች ነበር። አንደኛ፣ የሀገር ሽማግሌዎቹ ችግሩ እንዳይባባስ ማህበረሰቡን በማግባባት እና የጋራ መግባባትን በመፍጠር ላይ አተኩረዋል።

ሁለተኛ፣ ለደረሰው ጉዳት እውቅና በመስጠት እንዲሁም ችግሩ በሽምግልና እንዲፈታ ወጥ አቋም ይዘው ከአባገዳዎች ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔን ለማምጣት ጥረዋል።

ሰላም በሀገር ሰርቶ ለመግባት የሚያስችል የሀገር ምሰሶ ነው የሚሉት የጌዲኦ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ከ1 ዓመት በላይ በፈጀ ያላሰለሰ ጥረት ማህበረሰቡ የሚፈልገውን ውጤታማ ዘላቂ ሰላም መፍጠር መቻሉን ይገልፃሉ።

ማህበረሰቡ ለሽምግልናው የሰጠው ከፍተኛ ግምት እና ያሳደረው እምነትም ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

በሽምግልናው ሂደት ለደረሰው ጉዳት እውቅና እና ለተጎጂዎች ካሳ የተሰጠ ሲሆን፤ ይህ እርምጃ የማህበረሰቡን ፍትህ የማግኘት ጥያቄ የመለሰ ነው።

በሽምግልና ወቅት ቅራኔን ከማባባስ ይልቅ እርቅና ሰላምን ማስቀደም፤ የግጭት አባባሽ ምክንያቶችን ከመነሻው ማስወገድ ይገባል ይላሉ የጌዲኦ ሀገር ሽማግሌዎች።

ሰላም የሀገር ሞሰሶ እንደመሆኑ  እንደ ሀገር ያጋጠሙ ችግሮችን በንግግር እና በሰከነ ውይይት መፍታት እንደሚገባም የሀገር ሽማግሌዎቹ ይመክራሉ።

ይህ የጌዲኦ የሀገር ሽማግሌዎች ተሞክሮ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለያየ ምክንያት ግጭት ሲከሰት፣ ባህላዊ እና ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን መጠቀም እንደሚገባ ማሳያ ሆኖ ይቀርባል።

በሜሮን ንብረት

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Gedio #traditionalpeacemaking