በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ የጥበቡን ዘርፍ ተወዳዳሪነት እና ጠቀሜታ የሚያሳድግ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ መነሻ ሰነድ ላይ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ ፖሊሲው በተለይ ለጥበብ የፈጠራ ባለቤቶች ሕጋዊ ከለላ በመስጠት ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ የሚያረጋግጥ ይሆናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ የጥበብ ዘርፉን የሚደግፍ ፖሊሲ ባለመኖሩ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዳልተቻለ አንስተዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ምሁራን እና ባለሙያዎችን በማሳተፍ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ መዘጋጀቱን አመላክተዋል። ይህም የመደመር መንግሥት ለጥበብ ዘርፉ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል።
ከለውጡ በኋላ የመደመር መንግሥት ከኮሪደር ልማት ጎን ለጎን በርካታ የኪነ-ጥበብ ማዕከላትን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱንም ገልጸዋል።
ረቂቅ ፖሊሲው የጥበብና የፈጠራ ኢንዱስትሪ ሃብቶችን በማጥናት፣ በመጠበቅ፣ በማልማትና ተደራሽ በማድረግ ለዘርፉ ዕድገት እንዲውል የሚያስችል ነው ብለዋል።
በቀጣይ ረቂቅ ፖሊሲውን የሚያዳብሩ የተለያዩ ግብዓቶች ከተሰበሰቡ በኋላ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ እንዲፀድቅ ይደረጋል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።
ዘአማኑኤል መንግሥቱ