Search

በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ፣ ምርጫው በሚካሄድባቸው በሁሉም አካባቢዎች እንደሚወዳደር ኢዜማ አስታወቀ

ማክሰኞ ታኅሣሥ 07, 2018 333

በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው በሁሉም አካባቢዎች እንደሚወዳደር የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ

ኢዜማ ይህን ያለው በምርጫው ዙሪያ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ነው።

ምርጫ የፖሊሲ አማራጮችን ማቅረቢያ፣ የተረጋጋ መንግሥት መመስረቻ እና የዴሞክራሲ ባህል መገንቢያ መሳሪያ መሆኑን ያነሱት የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ኢዮብ መሳፍንት፥ ፓርቲያቸው ምርጫውን ለዚህ ዓላማ ብቻ ለመጠቀም እንደሚወዳደር ገልጸዋል።

ፓርቲው በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሕዝብን ድምጽ ለማግኘት ላለፉት 4 ዓመታት ሲዘጋጅ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ኢዜማ በሰላማዊ መንገድ ብቻ መንግሥት ለመሆን እንደሚሠራ የገለጹት ደግሞ የፓርቲው  ሊቀመንበር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (/) ናቸው።

መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ምርጫው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል።

በተለይ መንግሥት ምርጫውን ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባው ጠቁሟል።

መራጩ ሕዝብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ እና ሀሳብን መዝኖ እንዲመርጥ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከስሜት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ ታቅበው የመፍትሔ ሀሳብ በማቅረብ ዕድሉን በኃላፊነት እንዲጠቀሙ ፓርቲው መልዕክት አስተላልፏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ምርጫውን ከፍ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ኢዜማ ጠይቋል።

#ebcdotstream #Ethiopia #election #ምርጫ #ምርጫቦርድ #ኢዜማ