Search

ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ እና የደመቀ ባህል ያላት ሀገር ነች - የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

ማክሰኞ ታኅሣሥ 07, 2018 62

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ለመጡት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን ለይፋዊ ጉብኝት በመቀበሌ ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል።
“የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በሁለቱ ሀገሮቻችን መካከል እያደገ የመጣውን ትስስር የሚያመለክት ሲሆን ውይይቶቻችን በጋራ የቅድሚያ ጉዳዮቻችን ላይ ትብብሮቻችንን የበለጠ የምናጠናክርበት እንደሚሆን እምነቴ ነው።” ሲሉም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው፣ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አዲስ አበባ መግባታቸውን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአውሮፕላን ማረፊያ ስለተደረገላቸው አቀባበልም አመስግነዋል።
ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ እና የደመቀ ባህል ያላት ሀገር ነች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕንድ እና ኢትዮጵያ ጥልቅ የሆነ የሥልጣኔ ትሥሥር እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
“በተለያየ ዘርፍ ያለንን አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ከኢትዮጵያ አመራር ጋር ለመወያየት ተዘጋጅቻለሁ” ሲሉም ገልጸዋል።
የሁለቱ የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች በሁለትዮሽ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።
ሕንድ ጠንካራ የኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት አጋር ስትሆን 650 በላይ የሀገሪቱ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው እየሠሩ ይገኛሉ።
ሕንድ እ.አ.አ. በ2024/25፣ 476.81 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ያለው ሸቀጣሸቀጥ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከጠንካራ የንግድ አጋሮች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ነገ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
 
በላሉ ኢታላ