የመደመር መንግሥት ችግርን ለመፍታት ሕዝብን ማዳመጥ አስፈላጊ ነው የሚል ዕምነት አለው፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመላው ሀገሪቱ በሁሉም ከተሞች የልማት ሥራዎች ሲሠሩ፣ ያረጁት ሲታደሱ እና የተረሱ ዘርፎች ሲታወሱ ተመልክተናል፡፡
"ቃልን በተግባር በሚል መርህ" ከመንግሥት ባለፈ የማኅበረሰቡን ዘመን የተሻገረ በሰዓታት የተገደበ የሥራ ባህሉ እንዲሻሻል ሆኗል፡፡
በዚህ ሁሉ ክንውን ውስጥ የተሰሩ ስራዎች ‘ዜጎች በጠበቋቸው ልክ ናቸው ወይ?’ የሚለውን ለመረዳት የሚያስችል ብሎም ያሉ ክፍተቶች እንዲሞሉ የሚያደርግ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፤ እየተካሄደም ነው፡፡
በ24 ከተሞች በተደረጉት ውይይቶች ላይ ዜጎች በአካባቢያቸው የተደረጉ የልማት እና የአገልግሎት ተቋማት ሥራዎችን ገምግመዋል፡፡
በዚህም የቅርሶች እድሳት እና አዳዲስ የተሠሩ መዳረሻዎች ወደየአካባቢው የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ስለማድረጉ መስክረዋል፡፡
በዚህም የአካባቢዎቹን ገጽታ ከማሻሻል ባለፈ ለበርካቶች የሥራ እድል ስለመፈጠሩም ነው ነዋሪዎች የሚያነሱት፡፡

ሆኖም ከተሠሩ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ለመሆን ሰላም አስፈላጊ ስለመሆኑ ያነሱት ነዋሪዎቹ፣ የነበሩ ግጭቶች ስላስከተሉት ብክነትም አስታውሰዋል፡፡
ሕዝብ የሰላም ባለቤት ቢሆንም የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ሊቀጥል የሚገባው ስለመሆኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
የመሰረተ ልማት ግንባታን በተመለከተ በተለይም የተጀመሩ የመንገድ ሥራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የሚለው የዜጎች ሌላው ጥያቄ ሆኖ ቀርቧል፡፡
ከጉባ ብሥራቶች መካከል አንዱ የሆነው የመኖሪያ ቤት አቅርቦት አፋጣኝ ምላሽ የሚሻ መሆኑም በተወያዮች ተነስቷል፡፡

የምግብ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ የግብርና ዘርፍን ለመደገፍ እና ወጣቶች እንዲሳተፉበት ለማድረግ የተሠራው የማንቃት ሥራ መጠናከር እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ከአምራችነት ጋር ተያይዞም የተጀመሩ ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የጠቀሱት ተወያዮቹ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
የነዳጅ ድጎማ ጠቀሜታ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሌሎችም ውጤታማ የለውጡ ትሩፋቶች ተብለው በዜጎች የተጠቀሱ ናቸው፡፡
የንጹህ መጠጥ ውኃ እና የመብራት አቅርቦት፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የዋጋ ንረት፣ እንዲሁም የመንገድ የግንባታ ሥራዎችን ማስፋፋት ላይ እንዲሠራ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በመንግሥት እና ሕዝብ መካከል ያለውን ትስስር የሚያላሉ የብልሹ አሠራር ተሳታፊዎችን መንግሥት ሊያጤን እና እርማት ሊሰጥበት እንደሚገባም ኅብረተሰቡ አንስቷል፡፡
ሰላምን ዘላቂ ማድረግ እና የብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ላይ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ የገለፁት ነዋሪዎቹ፣ ያሉን ጥያቄዎች እንደሚመለሱ የተጠናቀቁ ሥራዎች ማሳያ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡
በአፎሚያ ክበበው