Search

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ሊካሄድ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ዓርብ ታኅሣሥ 10, 2018 41

በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችን እንደሚፈታ የሚጠበቀው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሊካሄድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
አካታች ለሆነው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ የውይይት አጀንዳዎችን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ ለኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በሰጡት መረጃ፥ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች እስከ ወረዳዎች የዘለቀው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት “ለካስ ስለ ሀገሬ እኔም መምከር እችላለሁ፤ ለካስ የኔም ድምፅ ይሰማል” ያሉ ዜጎችን ያገኘንበት ነው ብለዋል።
ስለ ሀገራቸው ባላቸው አመለካከትና አቋም ለረጅም ጊዜ ተገናኝተው የማያውቁ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድነት ቁጭ ብለው በጋራ መክረው ለሀገራዊ ምክክሩ የውይይት አጀንዳ መስጠታቸውን አንስተዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ግለሰቦች እና ተመራማሪዎች በግልና በቡድን እየመጡ የውይይት አጀንዳዎችን እንደሰጡም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ በመሳተፍ በዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚወክሏቸውን ሰዎች በፍላጎታቸው መምረጣቸውንም አውስተዋል።
ዜጎች በተወካዮቻቸው በኩል የሚሳተፉበት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚፈልጓትን ሀገር ለመገንባት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ ኢትዮጵያውያን ባለቤት ሆነው እንዲሳተፉና የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲወጡም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ጉባኤው ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት፤ የመነጋገርና የመደማመጥ ኢትዮጵያዊ እሴትን ለመመለስ ብሎም በሀገራችን የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር ያግዛል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰለጠነ ባህል የምትፈታ ሀገር እንድትሆን ያስችላታል ሲሉም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ጉባኤውን ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት እያጠናቀቀ እንደሚገኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ በተደረገ ውይይት መገለጹ የሚታወስ ነው።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋጅ መሠረት፤ በጉባኤው በህዝቡ የሚሰጡ የመፍትሄ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ያቀርባል፤ ለሕዝብ ይፋ በማድረግም አፈፃፀሙን ይከታተላል።
 
በየተመኙሽ አያሌው