Search

አርብቶ አደሯ የጥርስ ሕክምና ማዕከል ባለቤት

ረቡዕ ሐምሌ 30, 2017 151

የጥምር ሙያዎች ባለቤት ናት።
ባለቤቷ የጥርስ ሐኪም ሲሆን፤ እርሷ ደግሞ የዴንታል ቴራፒስት ናት። የጥርስ ሕክምና ማዕከል በመክፈት እየሰራች ትገኛለች፡፡
የጥርስ ሕክምና መስጫው ከተከፈተ 4 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡
እንስቷ አሁን ላይ የከብት እርባታን ላይ በመሳተፍ ስጋ ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ ላይ መሆኗን ትናገራለች።
ሙኒራ ጀማል በወጣቶች የማይደፈረው የከብት እርባታ ሥራ ላይ በመሳተፍ ላሞችን መንከባከብን ታዘወትራለች።
በቀን 2 ጊዜ ወተት በማለብ እና ለእንስሳቶቹ ምግብ በመስጠትም ረጅም ጊዜዋን እንደምታሳልፍ ነው የምታስረዳው፡፡
ከዚህ ቀደም የወተት ምርት በሀገሪቱ ላይ መቀነሱን ተከትሎ ስልጠናን በመውሰድ ወደ ሙያውም እንደገባችም ገልጻለች።
ወተትና የተለያዩ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን የምታቀርብበትን መሸጫ ሱቅ እንደከፈተችም ታነሳለች፡፡
 
 
 
አዳዲስ እና ሳይንሳዊ የእንስሳት እርባታ ዘዴዎችን እንደምትሞክት የምትናገረው ወጣቷ፤ ዘና ያረጋቸዋልና ላሞቿን ጃዝ ሙዚቃ ከፍታ እያስደመጠች እንደምታልባቸውም ትናገራለች፡፡
ሙዚቃ ያረጋጋቸዋል የምትለው ሙኒራ ከ 10 በላይ የሚታለቡ ላሞች እና ጊደሮች እንዳሉአት ታነሳለች፡፡
ከ4 በላይ ሥራዎችን እንደሞከረች የምታነሳው ሙኒራ፤ የሕክምና እቃ ከውጭ ሀገር በማስመጣት እና ዲያግኖስቲክ የምርመራ ማዕከል ከፍታ እንደነበር ታስታውሳለች።
በኋላም ገና የተወለዱ ወንድ ጥጃዎችን በርካሽ ዋጋ በመግዛት አደልባ በውድ እንደምትሸጥ ትናገራለች።
እንስሳት አርቢዎች አብዛኛውን ጊዜ ላሞቻቸው ወንድ ጥጃ ሲወልዱ እንደማይወዱ አንስታ፤ ነገር ግን ጥጃዎችን አደልቦ መሸጥ አዋጭ ቢዝነስ መሆኑን ታስረዳለች።
በሬ ከማደለቡ ጎን ለጎን ስጋቸውን ወደ ውጭ ሀገራትም በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘች መሆኑን ነው የገለጸችው።
ሚሊየነሯ ሙኒራ ተግቶ በመስራት ለውጥ እንደሚቻልም ለኢቢሲ ዶት ስትሪም ተናግራለች።
በሥራዎቿ አጋጣሚ በርካታ ፈታኝ እና ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ገጥመዋት እንደነበር አትዘነጋውም፡፡
“ዲያግኖስቲክ የምርመራ ማዕከሉን ስከፍት የመክሰር አጋጣሚ ተፈጥሮ፤ ሥራዎቼ ተበላሽተው ነበር” የምትለው ሙኒራ፤ ሰፊ የጥሞና ጊዜ በመውሰድ እና ስህተቶችን በማረም እንደ አዲስ ወደሥራ በመግባት ችግሮቿን እንደተቋቋመች ትናገራለች፡፡
በመሆኑም ሁሉም ሰው ተስፋ ባለመቁረጥ እና ሥራ በማክበር የሚፈልግበት ደረጃ መድረስ ይችላል ስትል ተናግራለች፡፡
 
 
በሜሮን ንብረት