Search

እየተለወጠ ያለው የቀይ ባሕር ቀጣና እና የኃይል አሰላለፍ

ረቡዕ ታኅሣሥ 15, 2018 728

ከስዊዝ ቦይ እስከ ባብ ኤል-ማንዳብ ሰርጥ ድረስ የሚዘልቅና 438 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የቀይ ባሕር ቀጣና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ምሕዋር እየተቀየረ እንደሆነ የሚያትቱት የትሪስቴ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር ፌዴሪኮ ዶኔሊ በፍጥነት ተለዋዋጭ እየሆነ መምጣቱን ያነሳሉ።

ቀይ ባሕር በዓለም ላይ ካሉት በጣም ተለዋዋጭ ቀጣናዎች ጋር የሚዋሰን ሲሆን፤ የአፍሪካ ቀንድ፣ የዓረብ ባሕረ ሰላጤ እና የኢንዶ-ፓሲፊክ አካባቢ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻዎችን የሚያገናኝ በጣም ወሳኝ ቀጣና ነው። ይህ የቀይ ባሕር ቀጣና በፍጥነት ተለዋዋጭ እየሆነ መምጣቱን የሚጠቅሱት ምሁሩ፣ ነባር እና አዳዲስ ዓለም አቀፍ ኃያላን በአካባቢው ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ እና ቁጥጥር ከፍ ለማድረግ እየተሽቀዳደሙበት ስለመሆኑ ዕለታዊ የዜና ፍጆታዎችን ዋቢ አድርገው ጠቁመዋል።

የምዕራባውያን የጂኦፖለቲካዊ ማዕከላዊነት ማሽቆልቆል፣ የአማራጭ ኃይሎች መነሳት እና የቀጣናው ተዋናዮች የቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴ ቀጣናውን ውስብስብ እያደረገው እንደሆነም ነው በጽሑፋቸው የጠቀሱት። ይህም መጻኢው ዓለም አቀፋዊ የኃይል ተዋረድ የሚፈተሽበት ውስብስብ እና ተለዋዋጭ መድረክ ፈጥሯል ይላሉ። አሁን ያለው የቀጣናው ሁኔታ በፈረንጆቹ 1989 በቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ላይ የተፈጠረውን የሊበራል ዓለም አቀፍ ሥርዓት እየተገዳደረ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የቀይ ባሕር ቀጣና ቀድሞ ከነበረው የአንድ ዋልታ ተጽዕኖ ወጥቶ ወደ ባለብዙ መድረክ ትብብር፣ ነጻ ገበያ መር ሥርዓት እና አካታችነትን ወደሚያራምደው አዲሱ አስተሳሰብ እየተሸጋገረ መጥቷል፡፡ እነዚህ አሁን እየተነሱ ያሉ መርሆዎች ደግሞ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በተፈጠሩት ውስጣዊ ድክመቶች እና ውጫዊ ተግዳሮቶች ተበላሽተው እንደነበሩ ጠቅሰዋል ዶኔሊ። በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ ፉክክር እየተጠናከረ መምጣቱን የሚጠቀሱት ምሁሩ፣ የድኅረ-ሊበራል የዓለም ሥርዓት እንቅስቃሴው ደግሞ ወደተለዩ ቀጣናዎች እየተስፋፋ መምጣቱን ጽፈዋል።

ሰፊው የቀይ ባሕር ቀጣና ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ዶኔሊ፣ አርክቲክ፣ ደቡብ ኢንዶ-ፓሲፊክ እና ባልካን ቀጣናዎችም የፉክክሩ መድረኮች መሆናቸውን ጠቁመዋል። የቀይ ባሕር ቀጣና ሥርዓትን ለማስከበር የሚያስችል ግልጽ የሆነ የበላይ ኃይል አጥቶ የቆየ በመሆኑ ተደራራቢ ፍላጎት ባላቸው አካላት መካከል ክፍት የፉክክር መድረክ እየሆነ መጥቷል።

ቀይ ባሕር ሜዲትራኒያን እና ኢንዶ-ፓሲፊክን የሚያገናኝ ለዓለም አቀፍ ንግድ እና ኢነርጂ የባሕር መንገድ የሆነ ስትራቴጂካዊው ባሕር ቀውስ ውስጥ ካሉት እንደ ሱዳን፣ ኤርትራ እና የመን ጋር መዋሰኑ ግን የሥጋት ቀጣና እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል። ቀጣናው የግጭት ቀጣና መሆኑ እና በአካባቢው ያሉ ሀገራት ደካማ መሆን ይህን በጣም አስፈላጊ የሆነ ባሕር ለከፍተኛ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት እና ፍትጊያ ክፍት እንዳደረገው ጠቅሰዋል፡፡

አሜሪካ እና ቻይና በቀጣናው ወታደራዊ ሰፈር እንዳላቸው የሚጠቅሱት ተመራማሪው፣ ሩሲያ በፖርት ሱዳን የጦር ሰፈር ለማግኘት እየሠራች እንደሆነ፤ የባሕረ ሰላጤው ኃያላን የሆኑት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና ኳታር በበኩላቸው በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላቸውን ይዞታ እያስፋፉ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ሀገራት በተለይ በሱዳን፣ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት እና በወታደራዊ ትብብር ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሆነ ምሁሩ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ፣ ኢራን እና እስራኤልም ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የጸጥታ ግንኙነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ምሁሩ ጽሑፋቸውን በመቀጠል በቀጣናው የለውጥ አንቀሳቃሾች የውጭ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የቀጣናው ሀገራት ጭምር እየሆኑ መምጣታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ከኢትዮጵያ እስከ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ግብፅ እና ሶማሊያ ያሉ የቀጣናው ተዋናዮች ስትራቴጂካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ዓለም አቀፋዊ ፉክክርን መቀላቀላቸውን ነው ያወሱት።

እነዚህ ሀገራት ለደኅንነታቸው ዋስትና ለማግኘት እንደ አሜሪካ፣ ቻይና እና ባሕረ ሰላጤው ተፎካካሪ ኃይሎች ጋር ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ አሰላለፋቸውን በመጠቀም በወታደራዊ እና ሌሎች ስትራቴጂካዊ መሠረተ ልማት ላይ እየሠሩ እንደሆነ አስታውሰዋል። ይህ ባለብዙ ዘርፍ-አሰላለፍ ለቀጣናው ተዋናዮች ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን ነው ምሁሩ የጠቀሱት። በሌላ በኩል እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ያሉት በሱዳን እና የመን ግጭቶች ውስጥ የየራሳቸው አሰላለፍ ያላቸው ሀገራት በተመሳሳይ ጊዜ ወደ አካባቢው መምጣት ለእጅ አዙር ጦርነት በር እንዳይከፍት ያሰጋል ባይ ናቸው።

ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ያጣችውን የባሕር በር ፍለጋ መጀመሯ በቀጣናው ያለውን አዲስ ዲፕሎማሲያዊ እና የደኅንነት ሁኔታ አዲስ ቅርጽ ውስጥ አስገብቶታል ይላሉ ጸሐፊው። እነዚህ እንቅስቃሴዎች የተበታተነውን ነገር ግን በተፈጥሮ የህልውና ትስስር ያለው የቀይ ባሕር ቀጣና እንዴት የድኅረ-ሊበራል ሥርዓት መነሻ እየሆነ እንደሆነ ማሳያዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

የቀይ ባሕር ቀጣና አሁን አሁን የዓለም ፖለቲካን ሰፊ ለውጥ ማሳያ እየሆነ ነው ይላሉ ምሁሩ። በቀጣናው እያቆጠቆጠ ያለው ሁኔታ አዲስ እና አንድ የኃይል ሚዛን ከማምጣት ይልቅ የምዕራባውያን ተጽዕኖ ማሽቆልቆል፣ ያልተማከለ እና ተወዳዳሪ ሥርዓትን ፈጥሯል ይላሉ። ቀይ ባሕር በቀጣናው ሀገራት እና በዓለም አቀፍ ኃይሎች፣ በመንግሥታት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተዋናዮች፣ እንዲሁም መደበኛ እና ኢ-መደበኛ ጥምረቶች መካከል ለአዳዲስ የመስተጋብር ዘይቤዎች መሞከሪያ እየሆነ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ነባሩ እና ምዕራባውያንን ያማከለው "ዓለም አቀፍ ሕግ" የሊበራል ሥርዓት የአንድ ዋልታ የኃይል ሚዛንን ያማከለ መሆኑን የጠቀሱት ዶኔሊ፣ አዲሱ የድኅረ-ሊበራል ሥርዓት ግን በተመረጠ ተሳትፎ፣ በሁለትዮሽ ድርድር እና በተለዋዋጭ አሰላለፉ የተለየ እና ተቀባይነት ያለው ስልት ይዞ መምጣቱን ጠቅሰዋል። ውጤቱም የአንድ ወገንን ሥርዓት ከማንበር ይልቅ መግባባት እና ሁሉን ያማከለ ፉክክር ላይ የተመሰረተ የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓት እየተፈጠረ እንደሚገኝ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በኃያላን መካከል ያለው ፉክክር አሁን በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል ሳይሆን በቀጣናዊ መድረኮች ላይ የተመሰረተ እየሆነ በመምጣቱ የቀጣናው ሀገራት አቅምም ወሳኝ እየሆነ መምጣቱን አውስተዋል። ወታደራዊ ተቋማት፣ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት እና ፖለቲካዊ ሂደቶች የአዲሱ ጥምረት ተጽዕኖ መፍጠሪያ መሣሪያዎች ሆነው እንደሚያገለግሉ ጠቅሰዋል።

ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉም የቀይ ባሕር ቀጣና ጉዳይ በአሜሪካ እና ቻይና፣ እንዲሁም በባሕረ ሰላጤው ኃያላን ፍላጎት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በቀጣናው ሀገራት ጥምረት ጭምር እየሆነ መምጣቱ እየታየ ነው ይላሉ "ዘ ኮንቨርሴሽን" ላይ ባሰፈሩት ሰፊ ሐተታ፡፡

 

በለሚ ታደሰ