በሐረር ከተማ ያየሁት ለውጥ አስገርሞኛል ሲሉ የመጀመሪያው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሐሰን ዓሊ ተናገሩ።
የመጀመሪያው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሐሰን ዓሊ በሐረር ከተማ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

አቶ ሐሰን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በተለይም ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ለአብነት የሚጠቀሱ ሥራዎች እውን ተደርገው ተመልክቻለሁ ብለዋል።
ቀድሞ የማውቃት ሐረር ፍጹም ተለውጣ፣ ተውባ፣ ዝናዋንና ታሪኳን በሚመጥን ደረጃ ልቃ አግኝቻታለሁ ሲሉ ገልጸዋል። በተለይም የቱሪዝም ሀብቶችን ከመጠበቅ ባለፈ ለጎብኚዎች ምቹና አስደሳች በሚሆን መልኩ የተሠሩ ሥራዎች ለሌሎች ከተሞችም ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም ከተማዋን ለማዘመንና ለነዋሪዎች ምቹ እንድትሆን ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ይበል የሚያሰኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሥራዎቹም ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት የሚሆኑ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
በከተማዋ በቀንም ሆነ በምሽት ለእግረኛና ለተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ምቹ የሚያደርጉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እውን መደረጋቸውንም አክለዋል።
በአመራሩ መካከል ያለው ቅንጅትና አንድነት እንዲሁም ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ መሠራቱ ለውጤቱ መገኘት መሠረት በመሆኑ፣ በቀጣይም ይህን ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን አቶ ሐሰን ዓሊ ገልጸዋል።
የመጀመሪያው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሐሰን ዓሊ ከ27 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው በቅርቡ መመለሳቸው ይታወሳል።