የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች ታላቁ የኢትዮጵ ኅዳሴ ግድብን በዛሬው ዕለት የጎበኙ ሲሆን፤ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ርስቱ ይርዳው ግድቡ እውን የሆነው ጥበብ የተሞላበት አመራር በመሰጠቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በርካታ ፈተናዎችን እያስተናገደች የቆየች ብትሆንም፤ ያሉባትን ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች በመቋቋም ዳግማዊ አድዋ የሆነውን የኅዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ያስመዘገበችው ድል የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ተግባር ምዕራፍ መሸጋረሩ የላቀ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን አመልክተዋል።
ምንም እንኳ አንዳንድ አካላት አሁንም የግድቡን ፋይዳ በግልፅ ባለመረዳት የተለያዩ ፕሮፖጋንዳዎችን እያሰራጩ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን እራሷን ከድህነት ለማላቀቅ እና ዜጎቿ የተሻለ የኑሮ ዘይቤ እንዲኖራቸው በማለም ያላትን እምቅና ተፈጥሮአዊ ሀብት የመጠቀም መብትን መሰረት በማድረግ እንዲሁም ፈተናዎችን ድል በመንሳት ግድቡን እውን ማድረግ ችላለች ሲሉ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ ተናግረዋል።
አቶ ርስቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ አሻራ ያረፈበት መሆኑን በመግለፅ፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞችም በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን ጠቁመዋል፡፡
አሁንም አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከተሰጠው ሀገራዊ ተልዕኮ በመነጨ ለግድቡ ደኅንነት የሚያደርገውን ክትትል እና ጥበቃ አጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በጉብኝቱ ተሳታፊ የነበሩ የአገልግሎቱ ከፍተኛ አመራሮች ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀውን ግድብ በቦታው ተገኝቶ መመልከት ልዩ ስሜትን ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል።
ታላቁን የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ለመገንባት ብዙ ተደክሞበታል የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ጥሪት ነው ያሉት የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፤ በቀጣይም ግድቡ ያለምንም የፀጥታ ስጋት ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት እንዲውል ማድረግ እና የሀገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የተቋሙ ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን ገልፀዋል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በመረጃ እና በደኅንነት ስምሪት ግድቡ ለታለመበት አላማ እንዲውል ቀጣይነት ያላቸው ስራዎች እንደሚሰራም ከፍተኛ አመራሮቹ መግለጻቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ አመልክቷል።