Search

በደላሎች እጅ የነበሩ 23 ሕገ-ወጥ ካርታዎችን በማምከን መሬቱ መልሶ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ተደርጓል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

እሑድ ታኅሣሥ 19, 2018 162

ዛሬ ማምሻውን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፣ መሪ ሎቄ አካባቢ ለሕዝብ ሁለገብ አገልግሎት የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ይህ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚያሳይ ሲሆን፤ ፕሮጀክቶቹ ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ፣ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ ለውድድር፣ ለዕረፍትና ለሕፃናት መጫወቻነት ምቹ ሆነው የተገነቡ መሆናቸውን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ በ10.5 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ለከተማችን ጽዳትና ውበት ተጨማሪ አቅም የፈጠረ ድንቅ ሥራ ነው ሲሉም ከንቲባ አዳነች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
 
ፕሮጀክቱ በውስጡ ያካተታቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች፦
• ሁለት ዘመናዊ የአዋቂዎችና የሕፃናት እግር ኳስ ሜዳዎች፣
• የቅርጫት ኳስ፣ የቴኒስና የመረብ ኳስን አጣምሮ የያዙ ሁለገብ ሜዳዎች፣
• በተፈጥሮ ድንጋይ ያጌጠ አስደናቂ ፋውንቴንና ፕላዛ፣
• በማራኪ አበባዎች ያማረ አረንጓዴ ስፍራ፣
• ጸጥ ያሉ የማንበቢያ ቦታዎች እና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣
• ሙሉ የመጫወቻ ቁሳቁስ የተገጠመለት የሕፃናት ማልሚያ (ECD)፣
• ዘመናዊ ካፌቴሪዎች፣
• ከ400 በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያ፣
• ለኤሌክትሪክ መኪኖች የኃይል መሙያ (EV Charger)፣
• የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣
• አካባቢውን በሥዕልና በቀለም ያስጌጡ የጥበብ ሥራዎች እና ወዘተ፤
 
ይህ ፕሮጀክት ያረፈበት መሬት፣ ቀደም ሲል በደላሎች እጅ የነበሩ 23 ሕገ-ወጥ ካርታዎችን በማምከን መሬቱ መልሶ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል የተደረገበት መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአካባቢው ነዋሪዎችና ወጣቶች በሥራ ዕድል ተደራጅተው የፕሮጀክቱ ዋነኛ ባለቤትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል።
መዲናችንን በየዕለቱ እየለወጥን፣ ቃላችንን በተግባር እያረጋገጥን እንቀጥላለን ሲሉም ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።