በአማራ ክልል የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ እና ዕውቅና መስጫ አዋጅ ቁጥር 298/2017 መሠረት፤ በክልሉ ምክር ቤት ለጸደቁ 15 የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ዛሬ በይፋ ዕውቅና ተሰጠ።
ለሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ዕውቅና መሰጠቱ የሀገር ሽማግሌዎች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ሕጋዊ ተቀባይነትና አስገዳጅነት እንዲኖራቸው ያስችላል ሲሉ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው ገልጸዋል።
ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች የዳኝነት አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸው ተጠሪነታቸው ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚሆንም ፕሬዝዳንቱ አመላክተዋል።
በዚሁ መሠረት ዕውቅና ተሰጥቷቸው ሥራ የጀመሩትና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙት 15 ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች፤ ሽምግልና፣ አበጋር፣ ረከቦት፣ ዱለት፣ አማሬ ቁና፣ አውሳይድ፣ ጎራው አባ አሊ፣ ስምንቱ ማይ ቤት፣ ዘወልድ፣ መዛርድ፣ ክፍሎ፣ ሰንዬሰገድ፣ አባ ሀጋ፣ ዙፋን ዋልዋጅ እና ሰባቱ ከዘራ ናቸው።
ቀድሞ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታወቁት እና አሁን ላይ ሕጋዊ ዕውቅና የተሰጣቸው የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች በክልሉ በሚገኙ ከ4 ሺህ በላይ ቀበሌዎች ላይ በስፋት ተግባራዊ እንደሚደረጉም ተገልጿል።
በተስፋሁን ደስታ