Search

የቀዳማዊ ልጅነት ክትትል - ለትውልድ ግንባታው ወሳኝ ኢንቨስትመንት

ረቡዕ ታኅሣሥ 22, 2018 60

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀዳማዊ ልጅነት ዕድገት ላይ ያተኮረ የአውደ ጥናት መድረክ በወራቤ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ፤ ቀዳማዊ ልጅነት ለምርታማነትና ለፈጠራ ሥራ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
መቀንጨርን ለማስቀረት በተከናወኑ የተቀናጁ የሥርዓተ ምግብ ሥራዎች ውጤት መገኘቱን ጠቁመው፤ በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።
በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በየዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሕዝብ ተሳትፎ እየተሰበሰበ ትምህርት ቤቶች ምቹ እየተደረጉ መሆኑን የገለጹት አቶ አንተነህ፤ በክልሉ በአሁኑ ወቅት 2 ሺህ 147 ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በቀጣይ አምስት ዓመታትም 1 ሺህ 525 ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ የቀዳማዊ ልጅነት ዕድገት ላይ ወሳኝ የሆነውን የትምህርት አቅርቦት ዕድል ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
የአፍሪካ ቀዳማዊ ልጅነት ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከበደ ወርቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የቀዳማዊ ልጅነት ዕድገት ክትትል ከጽንስ ጀምሮ እስከ 6 ዓመት ያሉ ልጆች የተሟላ የጤና እንክብካቤ፣ የመማር ዕድልና የተመጣጠነ ሥርዓተ ምግብ እንዲያገኙ የሚያስችል ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአካልና በአእምሮ የዳበረ፣ በመልካም ሥነ ምግባር የታነጸ፣ ጤናማና ብቁ ዜጋን ለማፍራት ለሕፃናት ዕድገት ወሳኝ የሆኑ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ማስፋፊያዎችን፣ የሕፃናት ማቆያዎችንና መጫወቻ ስፍራዎችን ማሟላት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመድረኩ በቀረበው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፤ የቀዳማዊ ልጅነት እንክብካቤን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ተመላክቷል።
 
በሕይወት አበበ