Search

የብልፅግና ጉዟችን ከሁሉም በሁሉም፣ ለሁሉም እንዲሆን እንሠራለን - አቶ አደም ፋራህ

ረቡዕ ታኅሣሥ 22, 2018 164

የብልፅግና የኢኮኖሚ አቅጣጫ ጉዞ ከሁሉም፣ በሁሉም፣ ለሁሉም እንዲሆን የማድረግ ሥራ እንሠራለን ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፣ በመደመር ፍልስፍና የሚመራው የመደመር መንግሥት በአራት ኢኮኖሚያዊ ሚናዎች ላይ አተኩሮ ይሠራል።
በዚህም የመጀመሪያው ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫን መተግበር መሆኑን አንስተው፤ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት፣ ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የኢትዮጵያን ብልፅግናን የሚያፋጥን ነው ብለዋል።
ሁለተኛው ብዝሃ ተዋናይ አቅጣጫ እንደሆነ ገልጸው፤ በኢኮኖሚ ውስጥ ሚና ያላቸው አካላት የተናጠል እና የጋራ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት መንግሥት ግንባር ቀደም ሚናውን እንደሚወጣ ጠቅሰው የግል ዘርፉ በማይሳተፍባቸው ዘርፎች መንግሥት ንቁ ኢንቨስተር እንደሚሆን አስረድተዋል።
ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፎች ያሉ አቅሞችን የመለየት፣ አቅሞቹን ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን ስልት መቀየስ እና አቅሞችን ለመጠቀም የሚያስችሉ የኢኮኖሚ አቅጣጫ መከተል ነው ብለዋል።
በዚህም መሰረት በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በአይሲቲ፣ በማዕድን፣ በግብርና ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ውጤት መምጣቱን አብራርተዋል።
ሦስተኛው ብዝኃ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ አቅጣጫ እንደሆነ ያነሱት አቶ አደም ኢኮኖሚው ሁሉም በፍትሃዊነት የሚጠቀምበት እና የሚሳተፍበት እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል።
በዚህም ለሁሉም እኩል እድል በመፍጠር ተሳትፎውን እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በማፋጠን ከውጤቱ ሁሉም በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ በመፍጠር የብልጽግና ጉዟችን ከሁሉም በሁሉም ለሁሉም የሆነ እንዲሆን የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በአራተኛ ደረጃ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን የማጠናከር አቅጣጫ እንደሆነ ገልጸው፤ ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ የሚቻለው ከሌሎች ጋር በመተባበር መሆኑን አስረድተዋል።
በኢኮኖሚ መተሳሰር፣ በጋራ ጥቅም ዙሪያ በጋራ መስራት፣ የኢኮኖሚ ውህደት መፍጠር እንዲሁም ፍትሃዊ ስርዓት እንዲኖር እና የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም ገበያ የተሻለ ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል በትብብር መስራት ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል።