አዲስ አበባን በአፍሪካ ለሕፃናት ማሳደግ ምቹና ተመራጭ ከተማ ለማድረግ የጀመርነው ሥራ ፍሬ እያፈራ ይገኛል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በከተማችን እየተተገበረ ባለው የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብር አማካኝነት፣ በየሰፈሩ የለየናቸው ውስብስብ እና ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያለባቸው 177 ሕፃናት እንደየጉዳታቸው ሁኔታ የተዘጋጁ ምቹ ዊልቸሮች ድጋፍ እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል።
ዊልቸሮቹ እንደየሕፃናቱ የአካል ጉዳት ሁኔታ ተስማሚ ሆነው መሠራታቸው ለሕፃናቱ ምቹና ውጤታማ ድጋፍ ለመስጠት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
ይህም የአካታችና ሁሉን አቀፍ ልማታችን አካል ሲሆን፣ ከተማችን ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ትሆን ዘንድ በቀጣይ ተደራሽ ያልሆኑ ሕፃናትን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።
ይህንን በጎ ተግባር ያስተባበራችሁና አብራችሁን በቅርበት እየሠራችሁ ያላችሁ አጋሮቻችንን፣ በተለይም የክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭን በተጠቃሚ ሕፃናትና ወላጆቻቸው ስም ከልብ አመሰግናለሁ ሲሉ ገልጸዋል።