የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ትልቅ የዕውቀት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ቤተ-መጻሕፍቱ አገልግሎት አሰጣጡን የሚያጎለብቱ የዲጂታል ሲስተሞችን አስጀምሯል።
በመድረኩም ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የቦርድ ሰብሳቢ ቡዜና አልቃድር እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት፥ የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን አስታውሰዋል።
ቤተ-መጻሕፍቱ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንስቶ በመዲናዋ ትልቅ የዕውቀት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በዕውቀትና በክህሎት የተካነ ትውልድ በማፍራት ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ መሰረት የሚጥል መሆኑንም አብራርተዋል።
ቤተ-መጻሕፍቱ አገልግሎት አሰጣጡን በአዳዲስ አሰራሮች በማላቅ እና የንባብ ባህልን በማዳበር የዕውቀት ሽግግር ድልድይ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ጥራ ያስጀመራቸው ዲጂታል ሥርዓቶችም የንባብ አገልግሎት አሰጣጥን በተሻለ አቅምና ጥራት ለማቅረብ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዲጂታል አገልግሎቶቹም የቤተ-መጻሕፍቱን የተቀናጀ አስተዳደር በማሳለጥ ለተመራማሪዎች የጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸውን ካሉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ ለማከናወን የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
በቀጣይም ነዋሪዎች የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በ24 ሰዓት አገልግሎት የፈጠረውን ምቹ የንባብ ምኅዳር ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
#EBC #ebcdotstream #AbrehotLibrary