በታህሳስ እና በጥር ወር የተለያዩ በዓላትን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ ለኢቢሲ በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ በርካታ ሕዝባዊና ሐይማኖታዊ በዓላት በድምቀት እንደሚከበሩ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት የገና በዓል በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ በምንጃር ሸንኮራ የጥምቀት በዓል፣ ጥርን በባሕር ዳር፣ የግዮን በዓል በሰከላ እንዲሁም የአገው ፈረሰኞች በዓል በእንጅባራ እንዲሁም የተለያዩ በዓላት በክልሉ በድምቀት እንደሚከበሩ ጠቁመዋል።
በእነዚህ በዓላት ላይ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች በብዛት የሚሳተፉ በመሆኑ፣ በዓላቱን በተገቢው መንገድ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ኃላፊው አብራርተዋል።
የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ምንም ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጥምረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በእነዚህ በዓላት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተስፋሁን ደስታ