ረቂቅ የኪነ-ሕንጻ ጥበብ የተንጸባረቀበትና ልዩ የምህንድስና ክህሎት የታየበት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መገኛ ናት - ላሊበላ ከተማ።
መስፈርቶችን በማሟላት እ.አ.አ. በ1978 በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መገኛ የሆነችው ላሊበላ ከተማ፤ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን፣ ከአዲስ አበባ በ645 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ትገኛለች።
ከተማዋ በየጊዜው ቱሪስቶችን ትቀበላለች፤ በቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም በየዓመቱ ታህሣሥ 29 ልዩ ክብረ በዓል ይከናወናል።
ዕለቱ የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ ልደቶች የሚከበሩበት በመሆኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነቱ ተከታዮች ዘንድ እንደ ድርብ በዓል ይቆጠራል።
የቅዱስ ላሊበላ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ መሳይ ወዳጀ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለጹት፤ ከተማዋ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበችው በውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ የሕንጻ ጥበብ ብቻ ሳይሆን፣ ሐይማኖታዊ በዓላቱን ልዩ የሚያደርጓቸው ክዋኔዎች ስላሏት ጭምር ነው።
የገና በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ አካባቢዎች በእግር፣ በአውሮፕላንና በመኪና በርካታ ሰው ወደላሊበላ ከተማ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ላሊበላ ከተማ መጓዝ ለሚፈልጉ ጎብኚዎች በቀን ከአራት እስከ አምስት ጊዜ የበረራ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በዓሉን ለማክበር ወደ ቅዱስ ላሊበላ ለሚመጡ እንግዶች አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የጠቀሱት ተቀዳሚ ከንቲባው፤ እንግዶች በምቹ ሁኔታ መስተንግዶ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዓሉን በማስመልከትም በመላው ዓለም ለሚገኙ ጎብኚዎች “ኑ የገናን በዓል በላሊበላ እናክብር” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
በላሉ ኢታላ
#ebcdotstream #EBC #lalibela