Search

በዓላት እና እምቅ የቱሪዝም አቅም

ማክሰኞ ታኅሣሥ 28, 2018 99

ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎችን ለመመልከት እና በዓላት ላይ ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በርካታ ጎብኚዎች እየመጡ ነው። በተለይም ከመስከረም እስከ ጥር ወራት የሚከበሩ በዓላትን አስታኮ ቱሪዝሙ ይበልጥ ይነቃቃል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ የቱሪዝም ልማት ሥራዎችም ኢትዮጵያ ያላትን ዘርፈ-ብዙ አቅም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መግለጥ ያስቻሉ ናቸው።
የቱሪዝም ባለሙያው አቶ አሸናፊ ካሳ፤ በአሁኑ ወቅት የጎብኚዎችን ቆይታ የሚያራዝሙ የተለያዩ አማራጮች በመስፋፋታቸው፣ ምቹ እና ማራኪ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መፈጠሩን ገልጸዋል።
አቶ አሸናፊ ከኢቲቪ አዲስ ቀን መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በተለይ የገና እና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቁመዋል።
በዘርፉ ሳቢ ሁኔታ በመፈጠሩና ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎች በመገንባታቸው የሚገኘው ጠቀሜታ ላቅ ያለ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቱሪዝም መዳረሻዎች በመበራከታቸውም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች "ጎብኚዎችን የት እንውሰዳቸው?" በሚል ሲያሳስባቸው የነበረው ስጋት ተወግዶ፣ ይልቁንም በርካታ ምርጫዎችን እንዲያቀርቡ ዕድል ፈጥሮላቸዋል ይላሉ ባለሙያው።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መልካሙ አዳም በበኩላቸው፤ የቅርስ ጥገና እና የማስዋብ ሥራዎች የመዳረሻዎችን ምቾት እና ተደራሽነት ማሳደጋቸውን አንስተዋል።
እንደ ገና እና ጥምቀት ያሉ በዓላት ደግሞ ለዘርፉ ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ የየአካባቢውን ባህልና ትውፊት እንዲሁም ኃይማኖታዊ ስርዓቶችን ለመመልከት የሚመጡ ጎብኚዎች መበራከታቸውንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አማካኝነት ለዓለም እያስተዋወቀች መሆኗን ጠቁመው፤ በእነዚህም ፕሮጀክቶች እንዲሁም በገበታ ለትውልድ መርሐ-ግብር ደረጃቸውን የጠበቁ ሪዞርቶች፣ ሎጆች እና መዝናኛዎች መገንባታቸው ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ማገዙን አመላክተዋል።
የቱሪዝም ልማቶቹ ከውብ ትውፊቶች እና ኃይማኖታዊ በዓላት ጋር ተዳምረው ለቱሪስቶች የማይረሳ ትዝታን ለመፍጠር እና የኢኮኖሚ ገቢን ለማሳደግ እንደሚያግዙም አቶ መልካሙ አስታውቀዋል።
 
በሜሮን ንብረት