እንስሳት እንደሰው ልጆች ሁሉ ለሙዚቃ ምላሽ እንደሚሰጡ እና ሙዚቃ እንሚያረጋጋቸው ይነገራል፡፡
ሙዚቃ እያዳመጡ የሚታለቡ ላሞች ላቅ ያለ የወተት ምርት እንደሚሰጡም አንዳንድ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
በመዲናችን አዲስ አበባ በከብት እርባታ ስራ ላይ የተሰማራችው ሙኒራ ጀማል፤ በቀን 2 ጊዜላሞቿን እንደምታልብ ትገልጻለች፡፡
ታዲያ ሙኒራ ላሞቿን ማለብ ከመጀመሯ በፊት ቀድማ የምታደርገው ነገር ቢኖር ለላሞቿ ለስለስ ያለ የጃዝ ሙዚቃ መክፈት ነው፡፡
ሙዚቃ ላሞችን ከማረጋጋት አልፎ የተሻለ ምርት እንዲሰጡ እንደሚያደርግ ስለተረዳሁ እኔም ይህንኑ ተግባር ሁልግዜ እተገብራለሁ ትላለች፡፡
በዚህም ቀድሞው ከማገኘው ሊትር መጠን በላይ ወተት ማግኘት ችያለሁ ስትል ነው ለኢቢሲ ዶት ስትሪም የተናገረችው፡፡
ሙኒራ መንግስት ባመቻቸላት ቦታ ላይ ከ10 በላይ ላሞች እና ጊደሮች እያረባች መሆኗን ገልጻ፤ የወተት ምርቷን ለመጨመር የተለያዩ ዘዴዎችን እንደምትጠቀም ነው የምታነሳው፡፡
በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ ባደረገው ጥናት ላሞችን በየቀኑ ክላሲካል ሙዚቃ እዲሙ በማድረግ ማለብ ጭንቀታቸውን በመቀነስ የወተት ምርታቸውን ከፍ እንደሚያደርገው አረጋግጧል፡፡
ከፈጣን ሙዚቃዎች ይልቅ ቀዝቀዝ ያሉ ሙዚቃዎች የበለጠ የወተት ምርታቸው ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው ጥናቱ ያመላከተው፡፡
በሜሮን ንብረት