የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች "እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ይደንቃል!" ይላሉ።
በቤተክርስቲያኒቱ አስተምሮ መሰረት እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ ሁሉን አሟልቶ በገነት ሲያኖረው በፈጣሪ እና በፍጡር መካክል ሕግ ለማኖር አንዲት ትዕዛዝ አዝዞታል። ይህቺ ትዕዛዝ አዳም ሁሉንም እንዲገዛ ነገር ግን ከአንዲት ዕፅ እንዳይበላ ነበር።
አዳም ግን እባብ ባሳተቻት ሔዋን ተመርቶ እንደ አምላክ አዋቂ ለመሆን ከዚያች ዕፅ በላ። ለሕጉ እና ለአምላክነቱ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔርም ትዕዛዙን አዳም እና ሔዋንን ከገነት አባረራቸው። ትዕዛዙን አፍርሰው ሲቀጣቸው ግን ዝም ብሎ ሳይሆን 5 ሺህ 500 ዘመን በኋላ ከራሱ ከአዳም ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል በመግባት ነው። ይህም የሚያሳየው እግዚአብሔር ትዕዛዙን ሲያፈርሱ መቅጣት እና ምሕረት ሲለምኑት ይቅርታ የባሕሪ ገንዘቡ እንደሆነ ነው አባቶች የሚያስተምሩት።
ቃሉን የማያጥፈው ፈጣሪም ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በዓለም ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ጨለማ ያስወግድ ዘንድ ፍጹም ሰው ሆነ። ከድንግል ማርያም የተወለደው ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ።
ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ 9 ቁጥር 2 "በጨለማ ውስጥ ለሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው” ያለው ይህን የክርስቶስን ሰውን ለማደን ከሰዎች መወለድን ለማመላከት እንደሆነ የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ።
ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግል ማርያም አማካኝነት የሰውን ሥጋ ለብሶ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሲሆን ሰው እና እግዚአብሔር፣ ሰው እና መላዕክት እንደታረቁ ይነገራል። ለዚህም ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ መላእክት በቤተ ልሔም መገኘታቸው ማሳያ እንደሆነ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ቁጥር 13 ላይ ተጠቅሷል።
እግዚአብሔር ከሰማይ ዙፋኑ ወርዶ እንደሰው በጨርቅ ተጠቅልሎ መገለጡ ነው አባቶችን አስደንቆ ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ሰው የሆነበት ጥበቡ ይበልጣል የሚሉት። "ሰው እና መላእክት፣ የተወለደው ክርስቶስን ያመሰግኑ ዘንድ ተባበሩ" በማለትም የሰው እና መላእክትን መተባበር ያመላክታሉ። ምክንያቱም በልደቱ መንፈሳውያን የሆኑት መላእክት እና ሥጋውያን የሆኑት የሰው ልጆች በአንድ ማኅበር፣ በአንድ ቃል "ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይገባል!" እያሉ በአንድነት እግዚአብሔርን አመስግነዋልና።
በአዳም ኀጢአት ምክንያት ፈርሶ የነበረው የመላእክት እና የሰው ልጆች ማኅበር ከተቋረጠ ከብዙ ዘመናት በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንደ ገና ተጀመረ።
የመላእክት እና የሰው ልጆች አንድነት እንደማያቋርጥ እና በሰማይም እንደሚቀጥልም፣ "በእኛ በደቂቀ አዳም እና በቅዱሳን መላእክት መካከል ልዩነት የለም" በማለት አረጋዊ መንፈሳዊ በተሰኘ የቤተክርስቲያን መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል።
ከቤተክርስቲያን ሊቃውንት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ስለ ክርስቶስ ልደት በመገረም ፣ "ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን አስቀድሞ የነበረው እርሱ ሕፃን ሆኗልና፤ እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ፤ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚሆን፣ በዘለዓለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ፤ ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ፤ ኀጢአትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት፤ ይህን ወዷልና!" በማለት ተናግሯል።
የክርስቶስ ልደት፣ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ የተፈጸመበት በዓል ነው። ሰው ለሞት ከመገዛት የዳነበት፤ ጨለማ ተወግዶ የብርሃን የነገሠበት ነው። የሰው ልጆች ከመላእክት ጋር ኅብረት የፈጠሩበትም ነው።
የቤተክርስቲያን አባቶች ይህን አምላክ ለሰው ልጆች ይቅርታውን እና ምህረቱን ያሳየተበትን በዓል በፍቅር እና በይቅርታ ማክበር እንደሚገባ ያሳስባሉ። በተለይም ዓለም ችግር ውስጥ ባለችበት በዚህ ዘመን ሰዎች የተደረገላቸውን አስታውሰው ወደበጎው መንገድ እንዲመለሱም ያስተምራሉ። የሰው ልጅ የፈጣሪን ትዕዛዝ በመሻሩ በበደሉ ዘላለማዊ ቅጣት ሲገባው የተካደው ፈጣሪ ይቅር ካለው የሰው ልጆች እርስ በርሳቸው ይቅር መባባልን ገንዘብ ማድረግ እንዳለባቸውም ይመከራል። የዚህ በዓል ወናው መልዕክትም ፍቅር፣ ይቅርታ እና ኅብረት ነው።
በለሚ ታደሰ