የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የፈጣሪን ይቅር ባይነት እና ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ማሳያ ነው ሲሉ ከኢቲቪ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የገና በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ነው።
በክርስትና እምነት አስተምህሮ መሠረት፥ ለ5 ሺህ 500 ዘመን በዓለም ላይ ሠልጥኖ የቆየውን ጭለማ ያስወግድ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የስብከተ ወንጌል ኃላፊ መጋቢ ሀዲስ ባህረጥበብ አዱኛ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ለሰው ልጆች ይዞት የመጣው መድኃኒትን ነው፤ ዓለም ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ሕመምተኛ ነበርና ብለዋል።
አያይዘውም፥ የክርስቶስ ልደት በዓል የፈጣሪን ይቅር ባይነት እና ቃል አክባሪነት እንዲሁም ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር የሚያመለክት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት የወንጌል ሰባኪ አብርሃም ተክለማርያም (ዶ/ር)፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው ለሰው ልጆች ቤዛ ለመሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለሰው ልጆች ሁሉ ትሕትናን እና ዝቅ ማለትን የሚያስተምረው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሰው ልጆች ሁሉ ሊማሩበትና ሊተገብሩት የሚገባ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሐዋሪያዊ ሥራ ቢሮ አገልጋይ አባ ገብረመስቀል በበኩላቸው፥ የልደት በዓል የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ተገዢ ሆኖ ባለመኖሩ እግዚአብሔር ወደ እኛ የመጣበት ነው ብለዋል።
ገና እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች ሁሉ የሰጠበት ትልቅ የደስታ በዓል ነው ያሉት አባ ገብረመስቀል፤ በማህበራዊ ሕይወት፣ በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲሁም በችግሮቻችን ሁሉ በመተሳሰብ እና በመደጋገፍ በዓሉን ማክበር ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የደስታ በዓል እንዲሆን የሃይማኖት አባቶቹ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በቢታንያ ሲሳይ
#EBC #ETV #EBCDotstream #Ethiopia #Holidays #EthiopianChristmas #Genna