ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሊት የተወለደው በኃጢአት ጨለማ ውስጥ ለነበረው ዓለም ብርሃን ሆኖ መምጣቱን ለማብሰር እንደሆነ ክርስቲያኖች ሁሉ ያምናሉ።
ሌሊቱ አልፎ ቀኑ እንደሚተካ ሁሉ፣ የጨለማው የዲያብሎስ አገዛዝ አብቅቶ የጽድቅ ፀሐይ መውጣቱን የሚያመላክት ምስጢር ነው ብለውም ያስባሉ።
ልደቱ ባልተጠበቀ ሥፍራ መሆኑ፣ ንጉሥ ሆኖ ሳለ በበረት መገኘቱ፣ ለደካሞች እና ለተናቁት ቅርብ ስለመሆኑ እንዲሁም ቁሳዊ ሀብት ሳይሆን መንፈሳዊ ትሕትና ለድኅነት አስፈላጊ መሆኑን ማሳያ ተደርጎ ይታሰባል።
ይህም የሰው ልጅን ትሕትና ለማስተማር እና ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ እንደሆነ በማሰብ ምዕመናን ዛሬም አስተምህሮውን ይጠብቁታል።
የክርስቶስ ልደት በምክንያት እና በምስጢር የተከበበ፤ ለዘመናትም ሲጠበቅ የነበረ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ክስተት ለሰው ልጅ ድኅነት ያለውን ፋይዳ ይገልጻል። ጥቂቶችን እንመልከታቸው፦
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ፥ ክርስቶስ በቤተልሔም የተወለደው ነቢያት ቀድመው የተነበዩትን ትንቢት ለመፈጸም ሲሆን፤ የቤተልሔም ትርጉም "የእንጀራ ቤት" በመሆኑ የሕይወት እንጀራ መሆኑን ለማሳየት ነው።
ቤተልሔም የንጉሥ ዳዊት ከተማ መሆኗ ደግሞ እርሱም ከዳዊት ዘር የሚወጣው እውነተኛው መሲሕ መሆኑን ለሰው ልጆች ማረጋገጫ ሆኗል።
ክርስቶስ የተወለደበት ወቅት የሕዝብ ቆጠራ የሚካሄድበት ወቅት መሆኑ ደግሞ፣ ጌታ የዓለም ሁሉ ፈጣሪ ቢሆንም ለሥጋዊ ሥርዓትና ሕግ መገዛቱን ያሳያል።
በተጨማሪም ስሙ በምድራዊ መዝገብ እንዲጻፍ በማድረግ፣ የሰው ልጆች ስም በሰማያዊው የሕይወት መዝገብ እንዲሰፍር መንገዱን የከፈተበት ጥልቅ ምስጢር መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስተምራሉ።
ከቤተልሔም እስከ በረቱ፣ ከሌሊቱ ድባብ እስከ ሕዝብ ቆጠራው ድረስ ያሉት ሁኔታዎች ድንገተኛ ክስተቶች ተደርገው አይወሰዱም፤ ይልቁንም የእግዚአብሔርን ትሕትና እና ፍቅር የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው።
እነዚህ ሁኔታዎች ጌታ ሰውን ለማዳን ዝቅ ብሎ መምጣቱን እና በምድር ላይ ያለውን ሥርዓት ሳይንቅ ለሰው ልጆች አርዓያ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
ይህም ልደት ለሰው ልጅ አዲስ ተስፋን እና የዘለዓለም ሕይወትን ይዞ የመጣ ታላቅ የደስታ የምስራች እንደመሆኑ፤ የሰው ልጆች ሁሉ በምድራዊ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ተስፋም፣ ስንቅም ያደርጉታል።
በጥበቡ አስፋው
#ebcdotstream #Genna #jesus #ገና