በ2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮችና ዕጩዎች ምዝገባ ሂደት ስኬታማ እንዲሆንና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለማስቀረት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ የምዝገባ ሂደቱን ዘመናዊና ምቹ ለማድረግ የቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁሟል። ይህም መራጮችና ዕጩዎች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን መጉላላትና ተፅዕኖ ለማስቀረት፣ አካል ጉዳተኞች (ዓይነ-ሥውራን) ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመዘግቡ ለማስቻል፣ መራጮች ቋሚ መለያ ቁጥር እንዲኖራቸውና የመረጃ አያያዝን ሥርዓት ለማስያዝ ያለመ መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።
በዚህም መራጮች "ምርጫዬ" የተባለውን የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም ራስን በራስ የመመዝገብ አማራጭ ተመቻችቶላቸዋል ብሏል።
በተጨማሪም በምርጫ ጣቢያዎች ታብሌቶችን በመጠቀም በምርጫ አስፈጻሚዎች አማካኝነት የሚከናወን የምዝገባ ሥርዓት የተዘረጋ ሲሆን፤ የቀደመውን አሠራር በመከተል በአካል በመገኘት በእጅ (በማንዋል) የመመዝገብ አማራጭም መጠቀም እንደሚቻል ተመልክቷል።
የምዝገባ ጊዜን በተመለከተ ቦርዱ ቀደም ሲል የራስን በራስ ምዝገባ ከጥር 15 እስከ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ለማከናወን አቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ሁሉም የምዝገባ አማራጮች ከፍትሐዊነት አንጻር በተመሳሳይ ጊዜ መጀመር ስላለባቸው ምዝገባው ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም. እንዲከናወን ቦርዱ ወስኗል።
በመሆኑም ቦርዱ የምዝገባ ምርጫ ጣቢያዎችን ዝርዝር በሕጉ መሠረት ከምዝገባው ቀን አስቀድሞ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።