Search

በጎነት ሲፀና

ታሪኩ የጀመረው እንዲህ ነበር፤ ወቅቱ 1997 ዓ.ም ላይ ነው።
 
አንዲት እናት የእንቅርት በሽታቸውን ለመታከም በጅማ ሆስፒታል ቀዶ ጥገና እየተደረገላቸው ነው።
 
በቀዶ ጥገናው በመሐል ግን ተጨማሪ ደም እንደሚያስፈልጋቸው ይነገራል። በወቅቱ ደግሞ ደም ለጋሽ አልተገኘም።
 
እናም ከቀዶ ጥገና መስጫው ክፍል ውጪ የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች ለጋሽ ከተገኘ በሚል ከወዲህ ወዲያ ይሯሯጣሉ።
 
የዚህን ጊዜ የሐኪሞቹን ጭንቀት የተመለከተው የአምቡላንስ ሾፌር የነበረው ኤልያስ አብዲሳ ጉዳዩን በአግባቡ ተረድቷል።
 
እናም ለመጀመሪያ ጊዜ ደም በመለገስ የእኚህን እናት ሕይወት ለመታደግ ወሰነ።
 
 
 
እንደወሰነውም አደረገ፤ በዚህም መተካት የሚቻለውን ደም ለግሶ የማይተካውን የሰው ልጅ ሕይወት መታደግ ቻለ።
 
ኤልያስ በማግስቱ በጎ ነገር እየተመኘ ነበር እግሮቹ ወደ ሆስፒታሉ ያቀኑት።
 
አይኖቹም በሕይወቱ ለመጀመርያ ጊዜ በለገሰው ደም የተረፈችውን ነብስ ለማየት ቸኩለዋል።
 
ከስፍራው ሲደርስ ያቺ በደም እጦት ከሞት አፋፋ ደርሳ የነበረች ነብስ በደስታ ተሞልታ አገኛት።
 
የበርካታ ልጆች እናት የሆኑት ታካሚ በተሰጣቸው ሕክምና ከበሽታቸው አገግመዋል።
 
ከትላንቱ በተሻለ የመኖር ተስፋን ሰንቀው ቀና ብለው ሲመለከት ባደረግው መልካም ሥራም እጀግ መደሰቱን አይዘነጋውም። “እሰይ ደግ አደረግኩ” ብሎም ለእራሱ ተናገረ።
 
ታካሚዋ እናትም እንዲህ ብለው መረቁት “ሰው የከበደው ለአንተን ይቅለልህ፤ ክፉ አይንካህ ልጄ"። ኤልያስም ከዚያ ጊዜ ጅምሮ “የእኔ ደም እንዲህ ሰው ለማዳን ከዋለ በየጊዜው እለግሳለው” በማለት ቃል ገባ።
 
ኤልያስ አብዲሳ አሁን ላይ ኗሪነቱን በአጋሮ ከተማ አድርጎ ላለፉት 20 ዓመታት የገባውን ቃል በመጠበቅ ያለማቋረጥ ደም በመለገስ ላይ መሆኑን ይናገራል።
 
ደጋግ ልቦች፤ በጎ አድራጊዎች በየአካባቢው አሉ። ኤልያስም ከነዚህ በጎ ፈቃደኞች መካከል አንዱ በመሆኑ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ተግባር እያከናወነ ይገኛል።
 
በራሄል አብደላ