Search

ፓርቲዉ በወሰደው ቁርጠኝነት ክልሉ በአጭር ጊዜ የብልፅግና ተምሳሌት መሆን ችሏል - አቶ አደም ፋራህ

ረቡዕ ጥር 06, 2018 365

በብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የፓርቲ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሁለት ዓመት ከአምስት ወራት ተምሳሌት የሆነ ውጤት ማስመዝገብ የቻለዉ ፓርቲው በወሰደዉ ቁርጠኛ አቋም ነው፡፡
የተቋማትን ዝግጁነት በቅንጅት መምራት፣ ያለምንም የሰላምና የጸጥታ ችግር ወደ ሥራ መግባት፣ መደበኛ አገልግሎቶች ሳይቆራረጡ መቀጠላቸዉ፣ ክልሉ በፋይናንስ ራሱን መቻሉ፣ ፈጥኖ ወደ ሥራ መግባትና የማስፈጸም አቅም መገንባት መቻሉ አሁን ለተመዘገቡ ስኬቶች መሰረት መሆናቸዉን አብራርተዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ሁሉን አቃፊና ሁሉን አሳታፊ ኅብረ ብሄራዊ ፓርቲ መሆኑን የተናገሩት አቶ አደም ፋራህ፣ በሙሉ እይታና በጥራት የመደመር ዕሳቤን መሰረት በማድረግ አሰባሳቢ ትርክት መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ሁሉን አባላት ማብቃትና ብቁ አደረጃጀት መፍጠር ያለውን ፋይዳ በመረዳት ለዚህ ስኬት በትኩረት ተሰርቷል ውጤትም ተገኝቶበታል ብለዋል፡፡
በየደረጃዉ ብቁ የሆኑ ስትራቴጂያዊ አመራሮችን ለማፍራት በርካታ ስልጠናዎችን በመስጠት ሀገራዊ ለውጡን መሸከምና ማስቀጠል የቻለ አመራር መፍጠር እንደተቻለም አንስተዋል፡፡
እንደ ፓርቲ በሁሉም መስኮች በተመዘገቡ ስኬቶችና ድሎች የሕዝብ ቅቡልነት ማረጋገጥ እንደተቻለ ያብራሩት አቶ አደም ወጥነት ያለው ተቋማዊ ስርዓት መዘርጋት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
የአመራሩንና የአባሉን አቅም በስልጠና በመገንባት ወጥነት ያለውን ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት እንደተቻለም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
በግምገማ መድረኩ በፓርቲ ሥራዎች ባለፉት ስድስት ወራት በተመዘገቡ ስኬቶችና ውስንነቶች እንዲሁም በቀጣይነት ትኩረት በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ በስፋት ውይይት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡