ትላንት የጉልበት ሠራተኛ፣ የወጥ ቤት ረዳት፣ ሳይክል አከራይ፣ የታክሲ ረዳት እንዲሁም ልብሶችን በካውያ የሚተኩስ ታታሪ እና ሥራ ወዳዱ ሰው አሁን አዲስ የስኬት መንገድ ጀምሯል።
ከዓመታት በፊት 150 ሺህ ብር ከፍሎ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዓረብ ሀገር በስደት እንዲሄድ ከጓደኞቹ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ከብዙ የግል ጥረት በኋላ አሁን መክሊቱን አግኝቷል።
ዮሐንስ ቱፋ ተሰማ ይባላል፤ የተወለደው በአርሲ አሰላ በቆጂ አካባቢ ሲሆን በልጅነቱ በተለያዩ ግለሰብ ድርጅቶች ተቀጥሮ የጉልበት ሥራ ለመሥራት ቢሞክርም “አትችልም” ተብሎ ተባሯል።
የቀን ሥራ እየሠራ ከአብሮ አደግ ጓደኛው ገንዘብ ተበድሮ ብስክሌት ገዝቶ በማከራየት፣ በመሸጥ እና የብስክሌት ጥገና በመሥራት የሥራ ባህሉን በሂደት ማሻሻል መቻሉን ያስታውሳል።
በደብረሊባኖስ ከተማ ብስክሌት እያከራየ ሕይወቱን ለማሻሻል ጥረት በጀመረበት ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ በመከሰቱ ብስክሌት ማከራየቱን አቁሞ ወደ ገጠር ቢገባም የገጠሩ ሕይወት አልተሳካለትም።
ጓደኛው በአዲስ አበባ የታክሲ ረዳት ሆኖ እንዲሠራ በፈጠረለት ዕድል በመጠቀም የመኪና ረዳት ሆኖ እየሠራ እያለ መኪናው ጋራዥ ገብቶ በመቆየቱ የሾፌሩ አክስት ጋር የልብስ ስፌት እና የካውያ ሥራ ለመሥራት ተቀጠረ።
የተሰፉ ልብሶችን በካውያ እየተኮሰ የሥራ አጋሩ እንደእሱ የልብስ ስፌት ሥራ እንዲማር ይገፋፋዋል። ልብስ ከሚሰፉ ሠራተኞች ጋር በመጠጋት ሥራውን መማር ይጀምራል። በአጭር ጊዜ ውስጥም የተለየዩ ስፌት ሥራዎችን በደንብ መሥራት እንደቻለ ይናገራል።
በልብስ ስፌት ቤቱ በካውያ ልብስ ከመተኮስ ሥራ ጎን ለጎን የልብስ መስፋት ሥራውን ልቅም አድርጎ ማወቅ በመቻሉ በመርካቶ ተቀጥሮ ለወራት የተለያዩ አልባሳትን መሥራት መጀመሩን ያስታውሳል።
ከዚያም በመቀጠል ወደ ሸጎሌ በማምራት ዘመናዊ የመጋረጃ ስፌት የሚሠራ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ መሥራቱን ይቀጥላል። በጥቂት ሳምንታት ውስጥም የመጋረጃ ስፌት ሥራውን በጥራት በመሥራት ራሱን እንደሚችል በአሠሪው ይነገረዋል።
በቆይታው ከሚከፈለው ደመወዝ በላይ ሙያውን በደንብ በመማር የራሱን ሥራ መጀመር እንደሚችል እምነት እንዳደረበት ይናገራል።
በአንድ ዓመት ውስጥም ሁሉንም የመጋረጃ ሥራ በራሱ በጥራት መሥራት እንደሚችል አረጋገጠ። ከሚከፈለው ደመወዝ እቁብ እየጣለ አጠራቅሞ ሁለት ማሽኖችን ገዝቶ ሸጎሌ አካባቢ የራሱን የልብስ ስፌት መደብር ከፍቶ እየሠራ ይገኛል።
ማንኛውም ሰው የሚሠራውን ሥራ ከልቡ የሚወድ ከሆነ ውጤታማ መሆን እንደሚችል የሚናገረው ወጣቱ፣ እዚህ የደረሰውም በጠንካራ የሥራ ባህል እንደሆነ ይገልጻል።
ማንኛወም ሰው ተቀጥሮ ሲሠራ ደምወዝ ብቻ ሳይሆን መጀመሪያ ሙያን ለመማር ከልቡ መጣር እንዳለበትም ይመክራል።
ወጣቱ ከተቀጠረበት ድርጅት ሙያን ተምሮ የራሱን ድርጅት መክፈት በመቻሉ ውብ የአልጋ ልብስ፣ አንሶላ፣ ትራስ እና የትራስ ጨርቆችን መሥራት ችሏል።
ተቀጣሪነት ሙያን ተምሮ የራስን ሥራ ለመሥራት ልምድ መሠረት ነው የሚለው ወጣት ዮሐንስ፣ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት መጀመሪያ ለሥራ ፍላጎት መኖር እንደሚያስፈልግ ያምናል። ሥራን መውደድ እና ማክበር የሚችል ሰው ውጤታማ መሆን እንደሚችልም እምነቱ ነው።
ከዓመታት በፊት ከ150 ሺህ ብር በላይ ከፍለው በሕገ ወጥ መንገድ በስደት መሄድ የመረጡ ጓደኞቹ አሁን ምንም ሃብት መፍጠር አልቻሉም።
ወጣት ዮሐንስ ቱፋ ግን ሙያን በጥረት ተምሮ ገንዘብ አጠራቅሞ ሁለት ዘመናዊ የልብስ ስፌት ማሽን ገዝቶ ሕይወቱን እየመራ ይገኛል።
ወጣቱ የጀመረውን የስኬት መንገድ በማስፋት ወደፊት ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሕልም እንዳለው ተናግሯል።
በላሉ ኢታላ