Search

የአርቲስት ነፃነት ወርቅነህ አጭር የሕይወት ታሪክ

እሑድ ጥር 10, 2018 363

አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ አዲስ አበባ ኡራኤል አካባቢ 1975 ዓመተ ምህረት ተወለደ።

ተዋናይ፣ ኮሜዲያን፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ በኢትዮጵያ የፊልም እና የቴሌቪዥን ታሪክ ውስጥ የራሱን ልዩ የሆነ የአቀራረብ ስልት እና የትወና ጥበብ በማሳየት የሚታወቅ ባለሙያ ነበር።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ ለቴአትር ጥበብ ራሱን የሰጠ እና በዚህም ለከፍተኛ ደረጃ የደረሰ አርቲስት ነበር።

ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ የራሱን ቴአትር በመድረስ እና ሴት ገጸ ባህሪን ወክሎ በመተወን ጭምር ተሰጥኦውን ያሳየው አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ፤ ይህን ችሎታውን በጠዋቱ የተረዱት የዚያኔው የአማርኛ መምህሩቲቸር’ ተሻለ ካበረታቱት በኋላ በቴአትር ሙያ እንደገፋበት በተለያዩ መድረኮች ይናገር ነበር።

በዩኒቨርሲቲ የቴአትር ክፍል ቆይታውም ከመምህራኑ ልዩ ድጋፍና አድናቆት ይቸረው ነበር።

በኪነ-ጥበብ መሳተፍ የጀመረው በወጣትነቱ ሲሆን፤ በተለይም በኮሜዲ ሥራዎቹ የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችሏል።

ከሠራቸው ሥራዎች መካከልፍሬሽማን’፤ ያንቺው ሌባ፤ ኤፍቢአይ እና ባለቀለም ሕልሞች ይጠቀሳሉ። 

ከፊልም ባሻገር ነፃነት በተለይ በኢቢኤስ (EBS) ቴሌቪዥን "የቤተሰብ ጨዋታ" የተሰኘውን ተወዳጅ ፕሮግራም ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን እያዘጋጀ ሲያቀርብ ቆይቷል።

የቤተሰብ ጨዋታ ፕሮግራም ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነት ያስገኘለት ሲሆን፤ ነጻነት በጥያቄ እና መልሶች አጋጣሚ ድንገት የሚፈጥራቸው ቀልዶች በተመልካቾች ተወዳጅ ነበሩ።

ሌላው በልዩ የንባብ አቀራረብ የሚሠራቸው ማስታወቂያዎች በሌሎች ላይ ያልታዩ ልዩ መታወቂዎቹ ነበሩ።

ነጻነት በስብዕናውም በሥራ ባልደረቦቹ ዘንድ ተወዳጅ የነበረ ሲሆን በትሕትናው፣ ለሥራ ባለው ትጋት እና ሁልጊዜም ሰውን ለማስደሰት ባለው ዝግጁነት የሚወደድ መሆኑን የፊልም ሙያ አጋሮቹ እና  የኢቢኤስ  የሥራ ባልደረቦቹ ይመሰክሩለታል።

#EBCDotstream #NetsanetWorkneh #Funeral