Search

የልጆችዎን የንባብ ባሕል ለማሳደግ ምን ያደርጋሉ?

የልጆችዎን የንባብ ባሕል ለማሳደግ ምን ያደርጋሉ?

****************

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአዳጊ ልጆችና ወጣቶች የንባብ ፍላጎት እየቀነሰ መምጣቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በአሜሪካ የሚገኝ ፒያ የምርምር ማዕከል ተቋም ይፋ ባደረገው ጥናት አስታውቋል።

እንደ ምርምር ተቋሙ ጥናት፣ 1980ዎቹ 13 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ አዳጊዎች በቀን ውስጥ እስከ 1 ሰዓት በንባብ ያሳልፉ እንደነበር ገልፆ አሁን ላይ ይህ አሃዝ እጅግ ቀንሶ ወደ 20 ደቂቃ ዝቅ ብሏል፡፡

ከዚህም ባለፈ 30 በመቶ የሚሆኑት አዳጊዎች በዓመት አንድም መፅሐፍ እንደማያነቡ ነው ጥናቱ ያሳየው፡፡

36 በሚሆኑ ሀገራት በተደረገ ተመሳሳይ ጥናት፣ እድሜያቸው 15 ዓመት ከሆናቸው አዳጊዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት መሰረታዊ የንባብ ችሎታቸው ደካማ ሆኖ ተገኝቷል።

በተጨማሪም የልጆች የንባብ ፍላጎት በአማካኝ በ20 በመቶ ቀንሷል ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) በበኩሉ፤ በተለይ በአፍሪካና ደቡብ ኤዥያ ሀገራት ከግማሽ በላይ ማለትም 60 በመቶ የሚሆኑ አዳጊዎች ምንም አይነት መፅሐፍ የሌላቸው መሆኑን ባደረገው ጥናት ገልጾ ነበር።

በዚህ መሰረት የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዳጊዎችና ወጣቶች ከመፅሀፍት ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅጉን አናሳ መሆኑን ነው፡፡

 እንደ አፍሪካና ደቡብ ኤዥያ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ የችግሩ መጠን ተባብሶ አብዛኛዎቹ ልጆች ምንም አይነት መፅሀፍ በቤት ውስጥ ማግኘት ባለመቻላቸው ከንባብ ጋር ሳይተዋወቁ እንደሚኖሩ ተገልጿል።

አጥኚዎቹ እንደሚገልፁት ልጆች ከሕጻንነት እድሜ ጀምሮ የንባብ ፍላጎት እንዲያድርባቸው እየተደረገ ካላደጉ የንቃተ ሕሊና ችግር እንዲሁም የአስተሳሰብ አድማሳቸውን ሰፊ እንዳይሆን ያደርጋል።

ለዚህ ችግር መባባስ እንደ ምክንያት ከተቀመጡት ነጥቦች መካከልም አንዱ ልጆች ከመፅሐፍት ይልቅ እንደ ቲክቶክ ላሉ  ሶሻል ሚዲያ ተጋላጭ መሆናቸው ነው።

ኮመንሴንስ ሚዲያ የተባለው ተቋም እንደሚገልፀው፤ በዚህ ዘመን ያሉ አብዛኛዎቹ አዳጊዎች ጊዜያቸውን በንባብ ላይ ከማዋል ይልቅ በአስደንጋጭ ሁኔታ በቀን እስከ 7 ሰዓት በቲክቶክ ላይ ያሳልፋሉ፡፡ ለንባብ ችሎታ አለመዳበርና ፍላጎት ማጣትም ዋናው ችግር አድርጎ አስቀምጦታል።

የማህበራዊ ሥነ-ልቡና ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሌላው ለልጆች የንባብ ፍላጎት ማጣት የወላጆች አስተዋፅኦ ትልቁን ቦታ ይይዛል።

የወላጆች የንባብ ፍላጎት አለመኖር ተፅዕኖው ከነሱ አልፎ በልጆቻቸውም ላይ የሚታይ ሲሆን አብዛኛዎቹ ልጆቻቸው ንባብን እንዲያዳብሩ ሲያደርጉ አይታዩም።

የልጆችን የንባብ ባሕል ለማዳበር ምን መደረግ አለበት ?

ምሁራን እንደሚገልፁት ለልጆች የንባብ ባሕል መዳበር ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ወላጆች ሲሆኑ ፣ይህንንም መሰረት በማድረግ የመፍትሔ ሀሳቦች አስቀምጠዋል፡፡

የመጀመሪያው ወላጆች በቀን ውስጥ 20 ደቂቃ የቤተሰብ የንባብ ጊዜ እንዲያመቻቹ ነው።

ይህ በየቀኑ ሊደረግ የሚችል የንባብ ልማድ ሕጻናትና አዳጊዎች ከመፅሐፍት ጋር እንዲለማመዱና የንባብ ፍላጎታቸው 30 በመቶ እንዲጨምር ያደርጋል።

ሌላው ለአዳጊዎች ስማርት ስልኮችን ከመስጠት ይልቅ መፅሐፍትን በቅርባቸው እንዲያገኙ ማድረግና ማንበብ እንዲችሉ መገፋፋት ነው፡፡

በትምህርት ቤቶች የንባብ ባሕልን ማስፋፋት

የመፅሐፍት እጥረት ባለባቸው ቦታዎች ዲጂታል ቤተ-መፅሐፍትን በመጠቀም ልጆች እንደ እድሜያቸው ፍላጎት ሊያሳድሩ የሚችሉ መፅሐፍትን እንዲያነቡ መጋበዝ ነው፡፡

አዳጊ ወጣቶች የማህበረሰብ ቤተ-መፅሐፍት አባል እንዲሆኑ ማድረግም ሌላው የንባብ ችሎታና ፍላጎትን የሚያዳብር መንገድ ነው።

የንባብ ባሕልን ማጎልበት ከትምህርት ውጤት ማምጣትና ማጣት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም።

ንባብ ከዚህም ባለፈ ልጆች የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው ብልህ፣ አሰላሳይ፣ ተመራማሪ እና የእውቀት አድማሳቸው የሰፋ እንዲሆኑ የሚያደርግ ወሳኝ  ጉዳይ በመሆኑ፣ ወላጆች ትኩረት ሰጥተው ልጆችን በሕጻንነት እድሜያቸው ከንባብ ጋር ማላመድ ይኖርባቸዋል።