ምክክር በልዩነቶች መካከል ድልድይ የሚገነባና ለዘመናት የቆዩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቅራኔዎችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ዓይነተኛ መሣሪያ ነው።
ከግጭት ይልቅ የመነጋገርን መንገድ መምረጥ፣ ለትውልዱ በመግባባትና በጋራ እሴቶች ላይ የተመሠረተ ጽኑ መሠረት ለመጣል ያስችላል።
ኢትዮጵያም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስብስብ ችግሮቿን በዘላቂነት ለመፍታትና የታሪክ ስብራቶቿን ለመፈወስ መመካከርን ዋነኛ ምርጫዋ አድርጋ እየሠራች መሆኗ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች አካታች ያደረገው የምክክር ሒደት፣ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ምክክርን በማከናወን መፍትሔዎችን እንደሚያመላክት ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ሀገራዊ ምክክሩ በዜጎች መካከል ያለውን መተማመን በማሳደግና አንድነትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ግጭቶችን ከምንጫቸው ለመፍታትና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሒደትን ለማጽናት ወሳኝ ሚና አለው። በመሆኑም የሚያጋጥሙ ማናቸውንም ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ በመመካከር የመፍታት ባሕል ሊዳብር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሀገራዊ ምክክር ሒደት ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ዝግጅቶችና ምዕራፎች ውስጥ የቆየ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ታሪክ በዚህ ደረጃና ልክ የተቋቋመ ገለልተኛ የምክክር ኮሚሽን ኖሮ እንደማያውቅም ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።
በመሆኑም የምክክር ኮሚሽኑ ተሻጋሪና ግዙፍ እሳቤ ሳይሰናከል ግቡን እንዲመታ እያንዳንዱ ዜጋ በንቃት ሊሳተፍበት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በዜጎች መካከል ያሉ መሠረታዊ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት፣ ዘላቂ ልማት እና ብሔራዊ መግባባት የሰፈነባት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ምክክሩ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የምክክሩ ውጤታማነት የሚለካው በሒደቱ አካታችነትና ግልጽነት በመሆኑ፣ የተፈለገውን ፍሬ እንዲያፈራ ሁሉም ዜጋ በንቃትና በባለቤትነት ስሜት ሊሳተፍ እንደሚገባ ኮሚሽነር ሙሉጌታ ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት