Search

በአማራ ክልል እስካሁን 13 ሺህ ታጣቂዎች በተሃድሶ ማዕከላት አልፈው ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል - ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን

ቅዳሜ ጥር 16, 2018 229

በኮምቦልቻ ጊዜያዊ የተሃድሶ ማዕከል ሲሰለጥኑ የቆዩ የቀድሞ ታጣቂዎች ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሽኝት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዲየር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው፣ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪን እየተቀበሉ መሆኑን ገልፀዋል።
በአማራ ክልል እስካሁን 13 ሺህ ታጣቂዎች በተለያዩ ዙሮች በተሃድሶ ማዕከላት አልፈው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን ብርጋዲየር ጄኔራል ደርቤ አስታውቀው፤ በጦርነት መፍትሔ ስለማይመጣ በውይይት ችግሮችን መፍታት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሃድሶ ሥልጠና ያጠናቀቁ ታጣቂዎች ማኅበረሰቡን በልማት ሥራዎች እንዲክሱ አሳስበው፣ የሚያነሷቸው ጥያቄዎችም በሀገራዊ ምክክሩ እንደሚፈቱ አመላክተዋል።
የሰላም ጥሪን የተቀበሉት የአፋሕድ ከፍተኛ አመራር ማስረሻ ሰጤ በበኩላቸው፣ ግጭቶች የመሠረተ ልማት ውድመት እና የኢንቨስትመንት መስተጓጎልን የመሳሰሉ ጥፋቶች ማስከተላቸውን አንስተው፤ በውይይት ወደ ሰላም መምጣት ጀግንነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ መመለስ ስለሚችሉ በጫካ ያሉ ወገኖች እንዲመለሱ የበኩላችሁን እንድትወጡ ሲሉም ለቀድሞ ታጣቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአማራ ክልል ከኮምቦልቻ በተጨማሪ በደብረ ብርሃን እና በጎንደር የተሃድሶ ማዕከላት የሰለጠኑ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማኅበረሰቡ እየተቀላቀሉ ሲሆን፣ የአሁኑ ሦስተኛው ዙር መሆኑ ተመላክቷል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ የሥነ ልቦና እና የአቅም ግንባታ ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን፣ የማቋቋሚያ ፋይናንስ ድጋፍ እንደተመቻቸላቸው ተመላክቷል።
 
በባዬ ሙላት