Search

የነገዋ ኢትዮጵያ በጋራ ትርክት ላይ ትገነባለች

ማክሰኞ ጥር 19, 2018 95

ትርክት የአንድ ሀገር ሕዝቦች ስለ ትላንት ታሪካቸው፣ ስለ ዛሬ ማንነታቸውና ስለ ነገ የጋራ ዕጣ ፈንታቸው ያላቸው ግንዛቤ ነው።

የጋራ ትርክት ለምን ያስፈልገናል? ብለን ብንጠይቅ፤ ልዩነቶችን እንደ ጌጥ የሚያይ ትልቅ ሀገራዊ ማዕቀፍ ለመገንባት፣ ዜጎች እኩል የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ለጠንካራ ተቋማት መሠረት ለመጣል እንዲሁም እኛ ማን ነን? ከየት መጣን? ወዴትስ እየሄድን ነው? ለሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ነው።

በጅማ ከተማ ፖለቲከኞች እና ምሁራን እንዲሁም ሃይማኖታዊና ማህበራዊ መሪዎች የተሳተፉበት "ሀገራዊ ትርክት ለምን? እንዴት? በማን?" የሚል ታላቅ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር በኢትዮጵያ በታሪክ፣ በአሁናዊ ሁኔታ እና በወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የተቀራረበ አመለካከት እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ በመድረኩ ተነስቷል።

መረጋጋትን በማስፈን ለዘላቂ ሰላም መሰረት ለመጣል፣ ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማትን ለመፍጠር እና ዜጎች በሀገራቸው ላይ እኩል የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ለማስቻል መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል።

ይህን እውን ለማድረግ የመደመር መንግሥት የቀየሳቸው አማራጮችን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ለመድረኩ አቅርበዋል።

ዕርቀ ሰላም እና ብሔራዊ መግባባት፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ የሃሳብ ፖለቲካ፣ ኢትዮጵያዊ የመግባባት ዴሞክራሲ እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አማራጭ ሆነው ቀርበዋል።

አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በበኩላቸው፥ መከፋፈል እና የክፍፍል እሳቤ ስለሚያስከትለው አደጋ አመላክተዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ ገለልተኛ የመንግሥት ሥርዓት ለመገንባት እና የሚከፋፍሉ እሳቤዎችን ለማቃናት ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ሥራዎች አብራርተዋል።

መገናኛ ብዙኃን በዚህ ዙሪያ ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸው የገለጹት ጋዜጠኛ ሙኒራ አብዱልመናን፤ ጥላቻና ክፍፍልን ከሚያባብሱ ዘገባዎች በመራቅ፣ ሀገራዊ አንድነትንና ሰላምን የሚሰብኩ ሥራዎችን ለሕዝብ ማቅረብ ይገባል ብለዋል።

ሙያዊ ገለልተኝነትን በመላበስ ሐሰተኛ መረጃዎችን መዋጋት ወሳኝ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ ከአጀንዳ ቀራጭነት ባለፈ የተግባቦት ድልድይ መሆን አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ከፋፋይ ትርክትን ወደ ኋላ በመተው የወል ትርክት እንዴት እንገንባ የሚለው ሃሳብ በጥልቀት ተነስቷል።

ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት ኢትዮጵያ ወዳለመችው ዕድገት እንድትሸጋገር መሰል የውይይት መድረኮች መጠናከር እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

በአፎሚያ ክበበው

#EBC #EBCDotstream #Ethiopia