አርሶ አደሮች ምርት ከመሰብሰብ ባለፈ በመዋጮዎቻቸው እሴት በማፍራት ላይ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በ1996 ዓ.ም የተመሠረተው የጊቤ ዴዴሳ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበር 207 የመጀመሪያ ደረጃ ማኅበራትን በማቀፍ 167 ሺህ ገበሬዎችን እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
አክለውም ማኅበሩ የግብርና ግብዓቶችን ከማቅረብ ተሻግሮ የምርት እሴትን ወደ መጨመር መሸጋገሩን ገልጸዋል።
ለዚህም እንደ ማሳያ የጠቀሱት ማኅበሩ በቅርቡ ያቋቋመውን ዘመናዊ የእህል ወፍጮ ሲሆን፣ ፋብሪካው በቀን 1 ሺህ 200 ኩንታል የበቆሎ ዱቄት የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል።
ይህ በ2.8 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ፋብሪካ ለአካባቢው ነዋሪዎች ሰፊ የጊዜያዊ እና የቋሚ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አስታውቀዋል።