በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች ጠንካራና ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ፌዴሬሽኑ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በአማራ ክልል ለሚገኙ የፌዴሬሽኑ አመራሮችና አባላት በባህር ዳር ከተማ የአሰልጣኞች ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ስዩም እንደገለጹት፣ ሥልጠናው ሴቶች በምርጫ ሥነ-ምግባርና መርሆዎች ላይ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ድርብ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በታዛቢነት እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ነው።
በተመሳሳይ የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ እንዬ ገነቱ፣ የታዛቢነት ሚናውን የሚወጡት ሴቶች ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆኑ፣ በዕውቀታቸው ብቁና አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ሰልጣኞቹም በምርጫው ሂደት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም በሐዋሳ፣ በጅማ፣ በአፋርና በደሴ ተመሳሳይ ሥልጠናዎችን የሰጠ ሲሆን፣ አሁንም በባህር ዳር የተጀመረው ንቅናቄ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና የሀገር ግንባታ ሚና ይበልጥ እንደሚያጎለብተው ተመልክቷል።