Search

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

እሑድ መጋቢት 13, 2018 58

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት እና የአየር መንገድ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በቦታው ተገኝተው ተመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት የከተማዋን ውበትና የትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ የሚሰሩ ስራዎች በጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኙ የገለጹ ሲሆን፣ በተለይም ከአሮጌው የዓባይ ድልድይ እስከ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የሚዘልቀው የ2 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ በአበረታች ሁኔታ መጀመሩን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም ከገብርኤል እስከ ምድረ ገነት የሚደርሰው የ1 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ መጠናቀቁንና ከአዲሱ የዓባይ ድልድይ ጋር የሚያገናኘው የ4 ኪሎ ሜትር የሃኒ ጋርደን - ወረብ አስፓልት መንገድም ለነዋሪዎች አገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ተመልክቷል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በባሕር ዳር ከተማ እያከናወናቸው ያሉ የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተጎበኙ ሲሆን፣ 91 በመቶ አፈፃፀም ላይ የሚገኘው የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በሚቀጥለው ወር ስራ እንደሚጀምር ይጠበቃል።
ዘመናዊ የመማሪያና የመኖሪያ ህንፃዎችን የያዘው ይህ ማሰልጠኛ ለዘርፉ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ሲሆን፣ በተያያዘም የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አዲስ ተርሚናል ግንባታ 81 ነጥብ 58 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
ይህ ተርሚናል ሲጠናቀቅ በሰዓት እስከ 1 ሺህ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለሀገራዊ ብልፅግና እና ለኢኮኖሚ እድገት ያላቸው ፋይዳ የላቀ መሆኑን በጉብኝታቸው ወቅት አስገንዝበዋል።
በአሸናፊ እንዳለ