7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኦሮሚያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምክር ቤት ገለጸ።
ምክር ቤቱ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደት ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያግዝ የምክክርና የስልጠና መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ገለጻ ያደረጉ ባለሙያዎች እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ በየጊዜው መሻሻሎችን እያሳየ መጥቷል።
በተለይም የለውጡ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የሃሳብ ብዝሃነት እንዲስተናገድ የምርጫ ሕጎች መሻሻላቸውና በምርጫ ቦርድ ላይ የተከናወነው ሪፎርም የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋቱን አንስተዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ይህንን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ግልጽ የፖሊሲ አማራጮችን ለመራጩ ሕዝብ ማቅረብና ዜጎች በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተመልክቷል።
ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ፓርቲዎች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም ተገልጿል።
የፓርቲዎቹ ተወካዮች በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ ያዘጋጀው መድረክ ለምርጫ ዝግጅታቸው ያለውን ፋይዳ አድንቀው፤ መንግሥት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በተለይም የተፈጠረውን የሚዲያ የአየር ሰዓት ዕድል በመጠቀም ለመራጩ ሕዝብ በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባም አመላክተዋል።
በመጨረሻም፣ ምርጫው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ቅድሚያ ለሰላም መስጠት እንደሚገባና ከምርጫው በኋላ የሚመጣውን ውጤት በጸጋ በመቀበል በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መዘጋጀታቸውን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።
በዘሃራ መሃመድ