የሥራ አጦችን ቁጥር ከመቀነስ አንጻር በርካታ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን የእራሳቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛል።
ኢቢሲ በአዲስ ቀን የጠዋት ገበያ መሰናዶ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ላይ የሚገኝ ተቋምን አስቃኝቶናል፡፡
ድርጅቱን ከመክፈታቸው አስቀድሞ በ12 ሀገሮች በመገኘት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ደግሞ 65 የሚደረርሱ በገጠር እና በከተማ አካባቢዎች በመጓዝ ጥናት ማካሔዳቸውን የበላይ አትክልት እና አስቤዛ ማዕከል መስራች አቶ በላይ ሞርዴ ገልፀዋል፡፡
በድርጅቱ የሚቀጠሩት ሰራተኞች ደግሞ ውል የሚገቡት ለ5 ዓመታት በድርጅቱ ለማገልገል ነው። ከዚያ ሙያ ለምደው እና ሰልጥነው የእራሳቸውን ንግድ ከፍተው እንዲወጡ ይገደዳሉ፡፡
ሰራተኞችን የእራሳቸውን ንግድ እንዲጀምሩ መነሻ እና መቋቋሚያ እንደሚመቻችላቸው ተመላክቷል።
የመሰረታዊ ፍጆታ ዕቃዎችን የሚያቀርበው ድርጅቱ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ ጤናማ ኢኮኖሚን ለመገንባት አላማ እንዳለው አቶ በላይ ይገልጻሉ።
ድርጅቱ የተለያዩ ዜጎችን ሚሊየነር ለማድረግ ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሆነም አቶ በላይ ሞርዴ ተናግረዋል።
በመሆኑም የድርጅቱ አሰራር ለሌሎችም ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑን ይገልጻሉ።
የድርጅቱ አላማ ባለቤቱን ሀብታም ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሥራ ፈላጊዎችን ቁጥር በመቀነስ ብዙ ባለሀብቶችን ማፍራት እንደሆነም ነው አቶ በላይ ያስረዱት።
በድርጅቱ ተቀጥረው የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች በድርጅቱ በተዘጋጀላቸው መኖሪያ ውስጥ እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡
ለገበሬውን ምርጥ ዘር ለማቅረብ፣ በመድሀኒት አጠቃቀም እና በአሰራር ለውጦች ላይ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ፣ ምርት በደረሰበት ወቅት በፍጥነት ወደ መሸጫ መደብሩ ለማምጣት የሚሰሩ ሰራተኞች እንዳሏቸው አንስተዋል።
ወደገበያው እንዳይገቡ የተከለከሉ እንዲሁም ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶች በመደብሩ እንዳይቀርቡ ጥናት በማድረግ ላይ የሚሰሩትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ30 በላይ ሰራተኞች እንዳሏቸው አቶ በላይ ሞርዴ ገልጸዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ