Search

ለግዙፉ የአውሮፕላን ማረፊያ የፋይናንስ አቅርቦት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሾፍቱ አቅራቢያ አቡሴራ አካባቢ አዲስ የሚያስገነባው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ሀገራዊ የመንገደኞች ማስተናገድ አቅምን 110 ሚሊዮን ማድረስ እንደሚያስችል ተመላክቷል።
ለዓለም አቀፍ አየር ማረፊያው ግንባታ የሚያስፈልገው ፋይናንስ ከየት ይገኛል?
ለግዙፉ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ 10 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ያሳወቀው አየር መንገዱ፤ ፋይናንሱን እንዲያፈላልግ የአፍሪካ ልማት ባንክን መርጧል።
ለዚህም እንዲረዳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ዛሬ ስምምነት አድርጓል።

 

 

 

ተቋማታቸውን ወክለውም የአየር መንገዱ ቺፍ ኮሜርሻል ኦፊሰር ለማ ያደቻ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳንት አኪንዉሚ አዴሲና (ዶ/ር) የፊርማ ሥነ ስርዓቱን አከናውነዋል።
የአየር መንገዱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በተገኙበት የተደረገው ስምምነት የተለያዩ አሰራሮችን የያዘ ነው።
በስምምነቱ መሰረት አየር መንገዱ ለፕሮጀክቱ ከሚያስፈልገው 10 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ የአፍሪካ ልማት ባንክ 80 በመቶውን ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የማፈላለጉን ኃላፊነት ወስዷል።
ለፕሮጀክቱ ከሚስፈልገው ወጪ 20 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሸፈን ይሆናል ተብሏል።
 

 
በሁለት ምዕራፍ የሚገነባው አዲሱ የአቡሴራ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት እጅግ ዘመናዊ ሲሆን፤ ይህም በአጠቃላይ እንደሀገር ከ110 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን በተሻለ ፍጥነት ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ እንደሚገነባም ነው የተገለፀው።
ፕሮጀክቱ በሚያርፍበት ስፍራ ለሚኖሩ 2500 አርሶ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በ350 ሚሊየን አሜሪካ ዶላር የመኖሪያ ቤት እና የመስሪያ ቦታ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።
ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባው እጅግ ዘመናዊው የአውሮፕላን ማረፊያ በ3975 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፤ በ2018 ዓ.ም ግንባታው እንደሚጀመር ይጠበቃል።
 
 
በላሉ ኢታላ