የጤና ሚኒስቴር በገጠራማ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ዛሬ አስተዋውቋል፡፡
ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እንዲህ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የዘመኑ የጤና ሥርዓት የሚጠይቀው አስፈላጊ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ "ላስት ማይል ኸልዝ" ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር "ሄፕ አሲስት" የተባለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን አስተዋውቋል።
ይህ ቴክኖሎጂ በተለይ በገጠራማ ኢትዮጵያ ርቀው በሚገኙ ዜጎች የተሻለ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ ያለመ ነው።
ቴክኖሎጂው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የምርመራና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደታቸውን በማገዝ፣ ባሉበት ሆነው ውጤታማ ሕክምና እንዲሰጡ ያግዛቸዋል ተብሏል።
ይህም የባለሙያዎችን በራስ መተማመን ከመጨመሩ ባሻገር፣ አላስፈላጊ የሪፈራል ሂደቶችን በመቀነስ ለታካሚዎችና ለቤተሰቦቻቸው ለህክምና የሚወጣን ወጪ ይቆጥባል ነው የተባለው።
እስካሁን ባለው በ7 ክልሎችና በ15 ወረዳዎች በሚገኙ 289 የጤና ኬላዎች ውስጥ የሚሰሩ 652 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
"ሄፕ አሲስት" ከሌሎች መሰል የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች የሚለየው፣ በጤና ሚኒስቴር ተቀባይነት ያገኙ ይፋዊ የሕክምና መመሪያዎችንና ማብራሪያዎችን መሠረት አድርጎ የተገነባ በመሆኑ ነው ተብሏል።
በብሩክታዊት ተገኝ