Search

የንፋስ ኃይል ለኢትዮጵያ ከብርሃን ባሻገር ያለው አስተዋፅኦ

ሓሙስ ሚያዝያ 08, 2018 97

የንፋስ ኃይል ልማት ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማሳደጊያ ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊ ብልጽግና እና ለዘላቂ ልማት መሰረት የሚጥል ስትራቴጂካዊ ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ ለሀገራችን የሚያበረክታቸው ዘርፈ-ብዙ ፋይዳዎች አሉት።

1.    የኢነርጂ ዋስትና እና የኃይል ምንጭ ስብጥር

የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት 90 በመቶ በላይ በውኃ ኃይል ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆኑ ለድርቅና መሰል ተፈጥሯዊ አደጋዎች ያለውን ተጋላጭነት ይጨምራል። ይህንን ስጋት ለመቀነስ የንፋስ ኃይል ስትራቴጂካዊ ፋይዳው የጎላ ነው። ይህምትክክለኛ ተዛማጅ’ (Complementarity) በሚባለው የተፈጥሮ ሚዛን ይገለጻል። በበጋው ወቅት የውኃ መጠን ሲቀንስ የንፋስ ፍጥነት የሚጨምር በመሆኑ የንፋስ እርሻዎች የኃይል መቆራረጥን በመከላከል ረገድ እንደ አስተማማኝ ዋስትና ያገለግላሉ።

2.      የኢንዱስትሪ መፋጠንና የሥራ ዕድል ፈጠራ

"ያለ አስተማማኝ ኃይል ኢንዱስትሪ፣ ያለ ኢንዱስትሪ ደግሞ ዕድገት አይታሰብም" እንደሚባለው የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች አቅራቢያ መገንባታቸው ለፋብሪካዎች የጀርባ አጥንት እየሆኑ ነው። ይህ ሂደት ሁለት ትልልቅ ስኬቶችን ያስመዘግባል፦

የዕውቀት ሽግግር፦ ግዙፍ የንፋስ ተርባይኖች በሚተከሉበትና በሚጠገኑበት ወቅት ለሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በቴክኒክና በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድና የሥራ ዕድል ይፈጠራል።

የምርት ዕድገት፦ ፋብሪካዎች በኃይል እጥረት ምክንያት ሥራ እንዳያቆሙ በማድረግ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ያሳድጋል። ይህም የገቢ ምርቶችን (Imports) በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ይረዳል።

3.    ቀጣናዊ ትስስርና የውጭ ምንዛሬ ግኝት

ኢትዮጵያ "የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል" (Energy Hub) የመሆን ታላቅ ራዕይ ያላት ሀገር ናት። የንፋስ ኃይልን በማልማት ለጎረቤት ሀገራት (ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ) የምትልከውን የኤሌክትሪክ መጠን ማሳደግ ትችላለች። ይህ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ከመፍጠሩም ባለፈ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በዘላቂነት ለመቅረፍ ይረዳል።

4.    አረንጓዴ አሻራና የአካባቢ ጥበቃ

የንፋስ ኃይል ምንም ዓይነት የካርቦን ልቀት የሌለው ንጹህ ምንጭ ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የጀመረችውን "አረንጓዴ ልማት" ስም ከማስጠበቁም በላይ ከአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ የፋይናንስ ድጋፍ እንድታገኝ ትልቅ በር ይከፍታል። በተጨማሪም የገጠሩ ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ በማድረግ፣ ለማገዶ የሚውል የዛፍ ጭፍጨፋን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ያስችላል።

የንፋስ ኃይል ለኢትዮጵያ የቅንጦት ምርጫ ሳይሆን የኢኮኖሚ ህልውና ጉዳይ ነው። ሀገሪቱ ያላትን ይህን ተፈጥሯዊ ፀጋ ወደ ኢኮኖሚያዊ ኃይል ለመቀየር የጀመረችው ጉዞ ተጠናክሮ ከቀጠለ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የንጹህ ኃይል ፋና ወጊ መሆኗ አይቀሬ ነው። ምክንያቱም ንፋስ ኃይል ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ አዲስ የተስፋ ብርሃንም ጭምር ነው።

ከጅምር እስከ ዛሬ፡ የስኬት ጉዞዎች

የኢትዮጵያ የንፋስ ኃይል ጉዞ በትልቁ የጀመረው 2005 . ጀምሮ ሲሆን እስከዛሬ ድረስ በሀገሪቱ የኃይል አውታር ውስጥ የሚከተሉት ግዙፍ የንፋስ እርሻዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

አዳማ 1 እና 2 በአጠቃላይ 204 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው እነዚህ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ኢትዮጵያ የንፋስ ኃይልን በስፋት መጠቀም እንደምትችል ያሳዩ የመጀመሪያዎቹ ግዙፍ ጣቢያዎች ናቸው፡፡

አሸጎዳ፦ በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ የተገነባውና 120 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ይህ ጣቢያ በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ትልቅ ግብዓት ሆኗል፡፡

አይሻ 2 በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው ይህ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ 80 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሲሆን ጣቢያው በኢትዮጵያና ጅቡቲ ድንበር አቅራቢያ የሚገኝ በመሆኑ ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር ጭምር ፋይዳው የጎላ ሆኗል፡፡

አሰላ (100 ሜጋ ዋት) በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሥራው ተጠናቆ ለምርት ዝግጁ የተደረገ ሲሆን ፕሮጀክቱ ዘርፉን በማሳደግና የአካባቢውን የኃይል ፍላጎት በመቅረፍ ረገድ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ለብሔራዊ የኃይል ቋት (Grid) የጀርባ አጥንት በመሆን እስከ 504 ሜጋ ዋት የሚጠጋ ኃይል እያቀረቡ ሲሆን እነዚህ ጣቢያዎች በተለይ በደረቅ ወቅት የውሃ ግድቦች መጠናቸው ሲቀንስ ክፍተቱን በመሙላት የኃይል መቆራረጥን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡

የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ

ቀደም ሲል የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች በመንግሥት ብቻ የሚከናወኑ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ባለሀብቶች በግልና በመንግሥት አጋርነት (Public-Private Partnership) ማዕቀፍ እንዲሳተፉ በሩን ከፍቷል፡፡ ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሆን ሽግግሩ መንግሥት ያለበትን የፋይናንስ ጫና በመቀነስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ መንገድ ጠርጓል፡፡

መንግሥት የኃይል ልማት ዘርፉን ለግል ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ የወሰደው የፖሊሲ ማሻሻያ በተጨባጭ ውጤት ማሳየት የጀመረ ሲሆን ለዚህም በሶማሌ ክልል የሚገነቡት የአይሻ 1 እና 3 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግል ዘርፍና በመንግሥት ትብብር (PPP) 300 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንፋስ ኃይል ልማት ለሀገር ውስጥ ብርሃን ከመስጠት ባለፈ ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚላከውን የኃይል መጠን በመጨመር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፡፡ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባትና የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ረገድ ኢትዮጵያ በንፋስ ኃይል የምታደርገው ጉዞ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡

የንፋስ ኃይል በኢትዮጵያ ያለበት አሁናዊ ደረጃ

ዓለማችን በታዳሽ ኃይል አማራጮች ላይ ያላትን ትኩረት ባሳደገችበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ የንፋስ ኃይል ልማት ቀዳሚ ተጠቃሚ ለመሆን በምታደርገው ጥረት ከፍተኛ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስትራቴጂካዊና መልክዓ-ምድራዊ ምቾት በመጠቀም የተፈጥሮ ሀብቶቿን ወደ ኃይል ለመቀየር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ስትሆን፣ በተለይም የንፋስ ኃይል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደገ የመጣውን የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማርካትና የኃይል ምንጮችን ስብጥር ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ሀገራችን በውኃ ሀብቷ "የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ" ተብላ እንደምትታወቀው ሁሉ በንፋስ ኃይል ረገድም ያልተነካ ግዙፍ ዕምቅ አቅም ያላት ሀገር ናት። ተፈጥሮአዊ የጥረትና መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ለኃይል ማመንጫነት ምቹ የሆኑ የንፋስ ኮሪደሮችን ፈጥሯል። ይህንን የተፈጥሮ ስጦታና ዕምቅ አቅም እንዲሁም በዘርፉ ላይ የታዩ አምርቾቶችን እንደምከተለው ማየት ይቻላል።

የተፈጥሮ ስጦታና ያልተነካው ዕምቅ ሀብት

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ሀገራት በንፋስ ኃይል እጅግ የበለጸገች ሀገር ናት። በተለይም በታላቁ ስምጥ ሸለቆ፣ በሰሜናዊ ተራራማ ቦታዎች እና በምሥራቃዊ የቆላማ ክፍሎች ያሉት የንፋስ ፍጥነቶች ለኃይል ማመንጫነት እጅግ ተስማሚ ናቸው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ እስከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት የንፋስ ኃይል የማመንጨት አቅም አላት። ይህ ግዙፍ አኃዝ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ካላት አጠቃላይ የኃይል ማመንጨት አቅም ጋር ሲነጻጸር፣ ዘርፉ ገና በደንብ ጥቅም ላይ ያልዋለና ሰፊ የልማት ዕድል ያለው መሆኑን ያረጋግጣል።

የንፋስ ኃይል ማመንጫ ዋና ዋና ነጥቦች

መሠረታዊ አሠራር፦ የንፋስ ግፊት በተርባይን ክንፎች (Blades) ላይ ሲያርፍና መሽከርከር ሲጀምር ከምላጮቹ ጋር የተያያዘውን ዘንግ (Shaft) እና የማርሽ ሳጥን (Gearbox) በማንቀሳቀስ ጄኔሬተሩ ኤሌክትሪክ እንዲያመነጭ ያደርገዋል።

የኃይል ሽግግር፦ በተርባይን አማካኝነት የንፋስ የእንቅስቃሴ ኃይል (Kinetic Energy) ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል (Electrical Energy) ይቀየራል።

የዘመናዊ ተርባይን ዋና ዋና አካላት፦ ተርባይን በዋናነት የሚሽከረከሩ ምላጮችን (Rotor Blades) ዘንግ (Shaft) የማርሽ ሳጥን (Gearbox) እና ጄኔሬተርን ያካተተ ነው።

የማመንጨት አቅም፦ የተርባይኖች መጠንና የምላጮቹ ስፋት እየጨመረ በሄደ ቁጥር፣ የሚሰበስቡት የንፋስ ኃይልና የሚያመነጩት የኤሌክትሪክ መጠን በተመጣጣኝ ሁኔታ ይጨምራል።

ዓለማችን ግዙፍ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች የት ይገኛሉ?

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን 350 ሺህ በላይ የንፋስ ተርባይኖች ተተክለው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል 7 ሺህ ተርባይኖችን የያዘው የቻይናው ጁኳን (Jiuquan) የንፋስ ኃይል ማመንጫ እርሻ 7 ሺህ 965 ሜጋ ዋት በማመንጨት ከዓለም ቀዳሚ ሲሆን፤ ሕንድና አሜሪካም በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የንፋስ ኃይል ምንነት እና ዓለም አቀፋዊ ዳራ

በዓለም ላይ የመጀመሪያው የንፋስ የኤሌክትሪክ ተርባይን የተተከለው .. 1883 ኦስትሪያ ቪየና በተካሄደ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሪክ ኤግዚቢሽን ፍሬደላንደር በተባለ ሳይንቲስት መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ይህ የፈጠራ ሥራ እየተሻሻለ መጥቶ .. 1887 ፕሮፌሰር ጄምስ ብሊዝ የተባለ ስኮትላንዳዊ የኮሌጅ መምህር 10 ሜትር ቁመት ያለው የንፋስ ተርባይን የጥጥ ጎጆውን ለማብራት የተጠቀመበት ሲሆን፣ ቀስ በቀስ ተደራሽነቱን በማስፋት በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መስጠት መጀመሩን የታሪክ ድርሳናት ከትበውታል።

የንፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታ በበርካታ ሀገራት ሙከራ እየተደረገበት ቆይቶ .. 1973 በዓለም ላይ የተከሰተው የነዳጅ ቀውስ ዘርፉን የበለጠ ማልማትና ማስፋፋት እንደሚገባ ትልቅ ግፊት ምክንያት ሆኗል።

ይህንን የነዳጅ ቀውስ ተከትሎ አሜሪካ መጠነ ሰፊ የንፋስ ኃይል ማመንጫ እርሻዎችን (Wind Farms) መገንባት የጀመረች ሲሆን .. 2008 ከዘርፉ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል 25 ነጥብ 4 ጊጋ ዋት ሊደርስ ችሏል።

የንፋስ ኃይል ማመንጫ ሂደት የንፋስን የተፈጥሮ እንቅስቃሴ ኃይል (Kinetic Energy) በተርባይኖች አማካኝነት ወደ ሜካኒካል በመቀጠልም ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀይር ቴክኖሎጂ ነው።

የንፋስ ተርባይን ክንፎች (Blades) በንፋስ ግፊት ሲሽከረከሩ ጄኔሬተሩን በማንቀሳቀስ ንጹህ ኃይል ያመነጫሉ፤ የሚመነጨው የኃይል መጠንም እንደ ተርባይኑ መጠንና እንደ ንፋሱ ፍጥነት የሚወሰን ይሆናል።

የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጥሬ ሃቆች

ፕሮጀክቱ የሚገኝበት አካባቢ፦ ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ኢተያ በተባለ ቦታ

ከአዲስ አበባ ያለው ርቀት፦ 150 ኪሎ ሜትር

ግንባታው የተጀመረበት ጊዜ፦ ታህሳስ 2014 .

ሥራ ተቋራጭ፦ ሲመንስ ጋሜሳ የተሰኘ የስፔን እና የዴንማርክ ኩባንያዎች በጥምረት

አማካሪ ድርጅት፦ ዳር አል ሃንዳሳህ ሺር እና ፓርትነር የተሰኘ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ኩባንያ ከታታ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ጋር በመተባበር

 

የግንባታ ወጪና የፋይናንስ ምንጭ፦ የፕሮጀክቱ ግንባታ በጥቅሉ 145 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የተከናወነ ሲሆን፣ ፋይናንሱም በዴንማርክ መንግሥት የተሸፈነ ነው።

የአካባቢው አማካይ የንፋስ ፍጥነት፦ 8 ነጥብ 2 ሜትር በሰከንድ

የማመንጨት አቅም፦ 100 ሜጋ ዋት

ዓመታዊ የኃይል ምርት፦ 354 ጊጋ ዋት በሰዓት

የተርባይን ብዛት፦ 29

የእያንዳንዱ ተርባይን የማመንጨት አቅም፦ 3 ነጥብ 465 ሜጋ ዋት

የተርባይን ተሸካሚ ምሰሶ/ማማ ቁመት፦ 84 ሜትር

የተርባይኑ ክንፍ ዲያሜትር፦ 132 ሜትር

የአንድ ተርባይን ክንፍ ርዝመት፦ 66 ሜትር

እስከ አሁን ከተገነቡ ተመሳሳይ ማመንጫ ጣቢያዎች ልዩ የሚያደርገው፦ የተርባይኖቹ የማመንጨት አቅም፣ የማማው እና የክንፎቹ ርዝመት ከፍ ያለ መሆኑ የኃይል ማመንጨት አቅሙንም የሚጨምር ይሆናል፡፡