Search

ኢትዮጵያ ከባሕር በር ተነጥላ እስከ ወዲያኛው ትኖራለች ብሎ የሚያስብ ሰው ካለ የዋህ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ሚያዝያ 07, 2018 72

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ወደኋላ የማይባል፣ በምንም ሁኔታ የማይቀለበስ እና የሀገራችን የኅልውና ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ልዩ ቆይታ፣ ይህንን የኅልውና ጉዳይ ወደ ጎን በመተው የሀገራችንን ብልጽግና ማሰብ እንደማይቻል አስገንዝበዋል።
ሀገራችን በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች በቀጥታ ተጋላጭ መሆኗን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በዚህ ቀጣና መሰማራት አለመቻሏ ፈታኝ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትላልቅ እና አቅም ያላቸው ሀገራት ከቀጣናው ደኅንነት ርቀው ከሄዱ፣ ትናንሽ ሀገራት ሰርጡን መጠበቅ ስለማይችሉ በዓለም አቀፍ ንግድ እና በቀጣናው ሰላም ላይ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያመጣ አስጠንቅቀዋል።
በመሆኑም የባሕር በር ጉዳይ በሰላም እና በድርድር የግድ ሊሳካ የሚገባው ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግሥት በአጭር ጊዜ እቅዱ የሎጂስቲክስ ወጪን ለመቀነስ እና ንግድን ለማቀላጠፍ በሞጆ እና ድሬዳዋ የደረቅ ወደብን ጨምሮ፣ የነጻ ንግድ ቀጣና፣ እንዲሁም የባቡር እና የፈጣን መንገድ መሠረተ ልማቶችን በስፋት እየገነባ መሆኑን አንሥተዋል።
ይህ እርምጃ ሀገራችን ከውጭ ለምታስገባቸው ዕቃዎች የምታወጣውን ወጪ በእጅጉ እንደሚቀንሰው ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ከረጅም ጊዜ አንጻር ዘላቂ የባሕር በር ካልተገኘ የሀገራችን ኢንዱስትሪዎች በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አብራርተዋል።
የምርት ጥራት፣ በጊዜው ገበያ ላይ መድረስ እና የሎጂስቲክስ ወጪ የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማነቆዎች መሆናቸውን አንሥተዋል።
እነዚህን በመቅረፍ ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ ለኢትዮጵያ ብልጽግና፣ ለቀጣናው የጋራ ዕድገት እና ለዓለም አቀፍ የንግድ ደኅንነት ወሳኝ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።
በለሚ ታደሰ