Search

መከላከያ ዩኒቨርሲቲ፦ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ እና የሉዓላዊነት አምባ

ቅዳሜ ሐምሌ 18, 2018 59

በዓለማችን ስኬታማ የሚባሉ ሀገራትን ታሪክ ስንመረምር ወታደራዊ የትምህርት ተቋማት ለሠራዊት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሁለንተናዊ የቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ ዕድገት የጀርባ አጥንት ሆነው እናገኛቸዋለን።

ለአብነት ያህል በአሜሪካ እንደ ዌስት ፖይንት ያሉት ወታደራዊ አካዳሚዎች እና በእስራኤል የታላፒዮት ወታደራዊ የትምህርት ፕሮግራም ለሀገራቱ መከላከያ ሠራዊት ዘመናዊነት ትልቅ ድርሻ የሚጫወቱ ናቸው። ከዚያም ባሻገር ለሲቪሉ ማኅበረሰብ የሚጠቅሙ እንደ በይነመረብ እና የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ግኝቶች መሠረት ጥለዋል።

ከዚህ አኳያ ጠንካራ ወታደራዊ ዩኒቨርሲቲ መገንባት ማለት ዘመኑን የዋጀ ሠራዊት ማፍራት ብቻ ሳይሆን የሀገርን የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ማለት ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ብቁ መኮንኖችን እና አመራሮችን በማፍራት ረገድ የጎላ ታሪክ ያለው ተቋም ነው።

በቅርብ ዓመታት በሠራዊቱ ውስጥ የተካሄደውን ሀገራዊ እና ተቋማዊ ሪፎርም ተከትሎ፣ ዩኒቨርሲቲው ከባህላዊ የጦር ትምህርት ቤትነት ባሻገር በምርምር፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ የልህቀት ማዕከል ወደ መሆን ተሸጋግሯል።

ይህ ሰፊ የሪፎርም ሥራ ተቋሙ የዘመኑን ወታደራዊ ሳይንስ ጠንቅቆ የተረዳ፣ በዕውቀት የሚመራ እና የቴክኖሎጂ ባለቤት የሆነ ሠራዊት ለመገንባት የሚያስችለውን አቅም እንዲፈጥር አድርጎታል።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚረዱ እጅግ ዘመናዊ የትምህርት ክፍሎችን አደራጅቶ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል የመከላከያ ምሕንድስና፣ የሳይበር ደኅንነት፣ ኤሮኖቲክስ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ወታደራዊ ሕክምና እንዲሁም የስትራቴጂክ አመራር ትምህርት ክፍሎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በእነዚህ ዘርፎች የሚሰጠው የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠና የሠራዊቱን የሰው ኃይል በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻል ላይ ይገኛል። ሠራዊቱን በጉልበት ብቻ ሳይሆን በአዕምሮ እና በዕውቀት ልዕልና እንዲዋጋ፣ እንዲሁም እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በብቃት እንዲያንቀሳቅስ በማድረግ ረገድ የዩኒቨርሲቲው አበርክቶ የጎላ ነው።

የተጨባጭ ምርምሮች እና የምርምር ውጤቶችን ወደ መሬት የማውረድ አቅም

ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት ባለፈ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራባቸው የምርምር ዘርፎች ውስጥ የጦር መሣሪያዎች ማሻሻያ፣ የመገናኛ እና ራዳር ቴክኖሎጂዎች፣ እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ይገኙበታል።

በእነዚህ የምርምር መስኮች በርካታ ተጨባጭ ግኝቶች ላይ መድረስ የቻለ ሲሆን፣ በተለይም የውጭ ሀገር ጥገኝነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ አቅም በማምረት እና በማሻሻል አስደናቂ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

የምርምር ውጤት በወረቀት ላይ ከማስቀረት ይልቅ ወደ ተጨባጭ ምርት እና አገልግሎት ለመለወጥ ዩኒቨርሲቲው እንደ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ ሆሚቾ ኢንጂነሪንግ እና ጋፋት አርማመንት ካሉ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች፣ የሠራዊቱ የኢንዱስትሪ እና የመሣሪያ ማምረቻ እንዲሁም የጥገና ተቋማት ጋር በጠበቀ ትሥሥር በመሥራት ላይ ይገኛል።

በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች የተዘጋጁ የዲዛይን እና የቴክኖሎጂ ፕሮቶታይፖች ቀጥታ ወደ እነዚህ የማምረቻ ተቋማት በመሸጋገር በስፋት እንዲመረቱ እና ለሠራዊቱ አገልግሎት እንዲውሉ ይደረጋል።

በተጨማሪም የጦር መሣሪያዎችን እና የከባድ ውጊያ ማሽኖችን የጥገና ጊዜ እና ወጪ ለመቀነስ የሚያስችሉ የሀገር ውስጥ መለዋወጫዎችን በራስ አቅም ማምረት ተችሏል። ይህም ቀደም ሲል ለከባድ ጥገናዎች ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማዳኑ ባሻገር ተቋሙ በራሱ አቅም የመታደስ እና የመጠገን ቴክኖሎጂ ባለቤት እንዲሆን አስችሎታል።

የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ላስመዘገቧቸው ልዩ ወታደራዊ እና የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ግኝቶች ሕጋዊ የፓተንት መብቶችን በተደጋጋሚ ማግኘት መቻላቸው፣ ተቋሙ በምርምር ዘርፍ ያለውን እውነተኛ ብቃት እና የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ በግልጽ የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።

ለሀገራዊ የፈጠራ ሥነ ምኅዳር ያለው አስተዋጽኦ

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ውጤቶች ለሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላ ሀገራዊ ዕድገት ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ ነው። ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች እና ፈጠራዎች ለሲቪሉ ኢንዱስትሪም ግብዓት በመሆን እያገለገሉ ሲሆን፣ ይህንንም ይበልጥ ለማጠናከር ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ምርምር እና ቴክኒክ ተቋማት ጋር ጠንካራ ትሥሥር ፈጥሯል።

ከሀገር ውስጥ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከቴክኒክ ተቋማት እንዲሁም ከኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽኖች ጋር በቅንጅት በመሥራት ጠንካራ ሀገራዊ የፈጠራ ሥነ ምኅዳር እንዲፈጠር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በተለይም በሳይበር ደኅንነት እና በሶፍትዌር ልማት ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች ለሀገራዊ የመሠረተ ልማት ጥበቃ እና ለሲቪል ተቋማት ዲጂታላይዜሽን ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በመላው አህጉሪቱ ቀዳሚ የወታደራዊ ቴክኖሎጂ፣ የሳይንስ እና የምርምር የልህቀት ማዕከል ለመሆን በጽኑ መሠረት ላይ ቆሞ እየሠራ ይገኛል።

ተቋሙ የሠራዊቱን የሰው ኃይል በዕውቀት ከማስታጠቅ ባሻገር ሀገራችን በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ራሷን እንድትችል በማድረግ፣ የውጭ ምንዛሬን በማዳን እና የብሔራዊ ደኅንነታችንን አስተማማኝነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለ ትልቅ የሀገር ኩራት ነው።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: