ኢትዮጵያ እንዴት ወደብ-አልባ ሆነች? ሴራ እና የሀገር ክህደት
ኢትዮጵያ እንዴት ወደብ-አልባ ሆነች? የ1983 ዓ.ም የሥልጣን ሽግግር ኢትዮጵያን ከባሕር በር በማራቅ ሀገርን ለማያቋርጥ የደኅንነት ስጋት ያጋለጠበት ወቅት ነበር።
የኢትዮጵያ ወደብ-አልባ መሆን ድንገተኛ የታሪክ አጋጣሚ ሳይሆን፣ በወቅቱ ሥልጣን በያዙት የሕወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎች ሆን ተብሎ የተፈጸመ፣ ሕጋዊ መሠረት የሌለው ውሳኔ ውጤት ነው።
የሥልጣን አልባነት እና የታሪክ ምጸት
የሴራው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሚጀምረው በሽግግሩ ወቅት ነው። በወቅቱ የፖለቲካ ሥልጣኑን በኃይል የተቆጣጠሩት፣ በለንደን ጉባኤ እና በሌሎች መድረኮች ኤርትራ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትገነጠል ፈቃዳቸውን ሰጡ።
እዚህ ላይ መስተዋል ያለበት ትልቁ የታሪክ ምጸት እና የሕግ ስተት፣ የባሕር በር አሳልፎ የመስጠት ውሳኔ የወሰነው አካል (የሽግግር መንግሥቱ) እንዲህ ዓይነት ዘላቂ እና ብሔራዊ ውሳኔ ለማሳረፍ የሚያስችል ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ ውክልና (ሥልጣን) ያልነበረው መሆኑ ነው።
ያለ ሕዝበ ውሳኔ፣ ያለ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ እና ያለ ጥልቅ ብሔራዊ ውይይት፣ በአንድ የታጠቀ ቡድን ፍላጎት ብቻ ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትጠቀምባቸው የነበሩትን፣ በተለይም እንደ አሰብ ያሉ ስትራቴጂክ ወደቦችን አጣች። ይህንን ውሳኔ ያሳለፈ ተጠያቂ የሚሆን ተቋም አለመኖሩ ደግሞ ጉዳዩን እስካሁን ድረስ አስገራሚ አድርጎታል።
በዚህ ውሳኔ ኢትዮጵያ ለዘመናት የነበራትን ቀጥተኛ የባሕር ንግድ መስመር እና ዓለም አቀፍ ተደራሽነት አቋረጠች።
የታሪክ ጥያቄ እና የአክሱም ሥልጣኔ ላይ የተፈጸመው ክህደት
ይህ ውሳኔ ያለ ተቃውሞ አልቀጠለም። በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ አንጋፋ ዐርበኞች እና የፖለቲካ ተንታኞች እና ዕድሉ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን በጽኑ በመቃወም፣ ሥርዓቱን ተጋፍጠውታል።
በተለይም ሻለቃ አድማሴ፣ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ኃይለማርያም የመሳሰሉ ምሁራን ያሰሙት የነበረውን አቤቱታ እና ድምፅ ትውልድ የሚዘነጋው አይሆንም። በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንም በይፋ አውግዘዋል።
የኢትዮጵያን ሕጋዊ እና ታሪካዊ የባሕር በር መብት መከበር እንዳለበት አጥብቀው ተከራክረዋል። የኤርትራ መገንጠል የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ፣ የጂኦ-ፖለቲካ እና የደኅንነት ጥቅም በጽኑ የሚጎዳ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
ይሁን እንጂ፣ የወቅቱ መሪዎች እነዚህን ተቺዎች ‘የፊውዳል ሥርዓት ርዝራዦች’፣ ‘የሰውን ሀገር ለመቀማት የሚቋምጡ ተስፋፊዎች’ በማለት በሶሻሊስታዊ ቀኖና አጣጥለውታል።
ይባስ ብሎም፣ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ እና የአክሱም መንግሥት የነበራትን የቀይ ባሕር ተጋሪነት መብት የሚገልጹትን ጥንታዊ የታሪክ ማስረጃዎች ‘ተረት ተረት’ በማለት አዲሱ ትውልድ ስለ ታሪኩ እንዳያውቅ አደረጉ።
የአክሱም ሥልጣኔ የባሕር ንግድ መስመሮችን በመቆጣጠር የደረሰበትን ከፍታ የሚዘክሩትን የታሪክ ሰነዶች ችላ በማለት፣ “አክሱም እስከ ባሕር ደርሳ አታውቅም” የሚል ታሪካዊ ክህደት እንደ መርሕ ይዘው ቀጠሉ።
ከ1983 በኋላ ያመለጡ ዕድሎች እና የሠላሳ ዓመቱ ቸልተኝነት
ኢትዮጵያ ወደብ-አልባ እንድትሆን የተደረገው በ1983ቱ ውሳኔ ብቻ አይደለም፤ ከዚያ በኋላም መብቷን ለማስከበር የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች ሆን ተብሎ እንዲባክኑ ተደርገዋል።
የአሰብ ራስ-ገዝ መዋቅር ችላ መባል፦ ደርግ ከመውደቁ በፊት ለአሰብ ልዩ የራስ-ገዝ አስተዳደር መዋቅር ዘርግቶ ነበር። ይህ መዋቅር ኢትዮጵያ ከኤርትራ መገንጠል በኋላም ቢሆን የአሰብን ወደብ ሕጋዊ ባለቤትነት ለመጠየቅ እንደ አንድ ጠንካራ መሠረት ሊያገለግል ይችል ነበር። ይሁን እንጂ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ይህንን ዕድል ሙሉ በሙሉ ችላ በማለት ወደቡን አሳልፎ ሰጠ።
የ1990-1992ቱ ጦርነት እና ታላቁ ክህደት
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተነሣው የድንበር ጦርነት፣ ኢትዮጵያ በኃይልም ሆነ በዲፕሎማሲ የወደብ መብቷን የምታስከብርበት ታላቅ ዕድል ተፈጥሮ ነበር። የኢትዮጵያ ሠራዊት በውጊያ መስክ የበላይነት ይዞ በነበረበት ወቅት፣ የአሰብን መግቢያ በሮች መቆጣጠር ይቻል ነበር።
የዓለም አቀፍ ሕግ ዕድል እና የአሜሪካ ፍንጭ
በወቅቱ እንደ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ያሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች በዝርዝር እንደተነተኑት እና መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የባሕር በር የማግኘት መብት ነበራት።
እንዲያውም፣ በወቅቱ የአሜሪካ መንግሥት ዲፕሎማቶች ሳይቀሩ ኢትዮጵያ ይህንን ሕጋዊ መብቷን በዓለም አቀፍ መድረክ እንድትጠይቅ ፍንጭ እና ዕድል ሰጥተው ነበር። ይሁን እንጂ፣ የኢሕአዴግ መሪዎች ይህንን ዕድል ለመጠቀም ፈቃደኛ አልሆኑም።
የባድመ ማደናገሪያ እና የአልጀርስ ስምምነት
የኢትዮጵያ ሠራዊት በውጊያ መስክ የበላይነት ይዞ የአሰብን በር ባንኳኳበት ወቅት፣ የወቅቱ መንግሥት የሕዝቡን ቀልብ ወደ ባድመ (የድንበር) ጉዳይ ብቻ በማዞር፣ የወደቡን ወሳኝ ጥያቄ አጠፋው።
በመጨረሻም በአልጀርስ የተፈረመው ስምምነት የኢትዮጵያን የወደብ መብት ሙሉ በሙሉ ችላ ያለ፣ የወደብ ጉዳይ ሐሳቡም እንዳይነሣ በግልጽ የተከለከለበት ባድመንም ሆነ የወደብ ዕድልን ያጣችበት “የዲፕሎማሲ ክሥረት” ሆነ።
ውጤቱ እና ዋጋው
በዚህ ተከታታይ ክህደት እና ያመለጡ ዕድሎች ምክንያት ኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት በባሕር ንግድ ለመሳተፍ ለጎረቤት ሀገሮች (በዋናነት ለጅቡቲ) በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ክፍያ ለመክፈል ተገድዳለች።
ይህ የኢኮኖሚ ደም-ፍሰት የሀገራችንን ዕድገት ገድቧል። ከዚህም በላይ፣ የባሕር በሯን ማጣቷ የጂኦ-ፖለቲካ ተፅዕኖዋን እና የብሔራዊ ደኅንነቷን አዳክሟል።
ይህ ብቻ ሳይሆን በኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ስለ ወደብ መናገርም ሆነ መጠየቅ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ችግር ተዳርገዋል። ወደብ ከማሳጣት በላይ ሐሳቡንም ማንሣት ወንጀለኛ የሚያስብልበት ሥርዓት መፈጠሩ የዘመን ውድቀት ያደርገዋል።
የትውልዱ መነሳት እና የማይቀረው ጥያቄ
የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና፣ የኢኮኖሚ ነጻነት እና የብሔራዊ ክብር ጉዳይ ነው። ያለፈው ትውልድ በሴራ ያሳጣውን መብት፣ የዛሬው እና የቀጣዩ ትውልድ በሰላማዊ፣ በሕጋዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማስመለሱ የማይቀር ነው።
ኢትዮጵያውያን መብታቸውን ለማስከበር ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ ነው። ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ፣ ትውልዱ እንቅልፉን ሊተኛ አይችልም። ይህ የትውልድ አደራ እና የሀገር ጥሪ ነው።
በአዶኒያስ ወልደ አረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: