Search

የ"ራሴን በጉያዬ፣ የሌላውን በጋራ" የግብጽ የሞኝ ብልጠት አካሄድ ዳግም ሲጋለጥ

ሰኞ ሐምሌ 20, 2018 42

 

ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ 85 በመቶ የምታመነጭ እና ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሕይወት እስትንፋስ የሆነች ሀገር ነች።

ይሁን እንጂ ግብጽ ይህንን የማይካድ የተፈጥሮ እውነት ወደ ጎን በመተው ለረጅም ዘመናት "የዓባይ ውኃ ብቸኛ ባለቤት እኔ ነኝ" የሚል የሞኝ ብልጠት ፖለቲካ ስታራምድ ኖራለች።

ካይሮ ይህንን የውኃ ሞኖፖል ለማስቀጠል መሠረት የምታደርገው ኢትዮጵያን ያገለሉትን እና ጊዜ ያለፈባቸውን 1929 እና 1959 የቅኝ ግዛት ዘመን 'ስምምነቶች' ነው።

ከዚህም አልፋ የውኃ ድርሻዬ የምትለውን ለማረጋገጥ በቀጣናው የውክልና ፖለቲካን በመጠቀም ሀገራት እርስ በርስ እንዲጋጩ፣ ትርምስ እንዲፈጠር እና ኢትዮጵያ በውስጥ ችግር ተተብትባ የራሷን ጸጋ እንዳትጠቀም የተለያዩ የሴራ ድሮችን ስታደራ መኖሯ የአደባባይ ምሥጢር ነው።

ለዘመናት የዓባይ ወንዝን በብቸኝነት ለመጠቀም ስትከተለው የቆየው ይህ አካሄድ ሀገሪቱ በዜሮ ድምር ስሌት የምትመራ እና ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድ መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ኢትዮጵያ ከደጇ የሚመነጨውን ተፈጥሯዊ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን ስታነሣ አምርራ የምትቃወመው ግብጽ፣ በቀይ ባሕር የባሕር ላይ ደኅንነት ዙሪያ ፍጹም ተቃራኒ የሆነ እና "ዐይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ" የሚል ሌላ የሴራ አካሄድ ይዛ ብቅ ማለቷ ነው።

የታችኛው ተፋሰስ ሀገር የሆነችው ግብጽ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ "የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ድምፅ እና ይሁንታ ሊኖራቸው ይገባል" በማለት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብት ስትገዳደር ኖራለች።

በተቃራኒው ግን በቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ ስትጠየቅ "ውይይት እና ውሳኔው የሚመለከተው የባሕሩ ተዋሳኝ ሀገራትን ብቻ ነው" የሚል የሞኝ ዜማ ማቀንቀን ከጀመረች ውላ አድራለች። ይህ ተቃራኒ እና ሚዛን የሳተ አካሄድ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማወናበድ እና የማይመስሉ ጥያቄዎችን በማንሣት ኢትዮጵያን ከጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ለማግለል ያሰላችው ያረጀ ስትራቴጂዋ ነው።

ይህንን የካይሮን የሚጣረስ እና የተፈጥሮ ሕግን የሚቃረን አካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከሁለት ዓመታት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ታሪካዊ ማብራሪያ በግልጽ አስቀምጠውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ ባሕር እና ዓባይ ከኢትዮጵያ ዕድገት እና ሕልውና ጋር በቀጥታ የተሣሠሩ መሠረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን በመጠቆም፣ ተፈጥሯዊ ትሥሥራቸውን አብራርተዋል።

ዓባይ ከኢትዮጵያ እየፈለቀ ለግብጽ የሕልውና ጉዳይ ከሆነ እና ስለ እርሱ በግልጽ መነጋገር ከቻለች 130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ታሥራ መኖር ስለማትችል ስለ ቀይ ባሕር መነጋገርም ሆነ መደራደር ነውር ሊሆንባት አይገባም ነው ያሉት።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል፣ ተፈጥሮ በውኃ አዙሪት ያስተሣሠረቻቸውን እነዚህን ሁለት የውኃ አካላት እና ጂኦ-ፖለቲካዊ እውነታዎች አንዱን የብቸኝነት ንብረት አድርጎ ሌላውን መከልከል ከፍትሕ እና ከተፈጥሮ ሕግ ጋር ፈጽሞ የሚጣረስ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ይህንኑ ጽኑ አቋም እና የግብጽን ግብዝነት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በሚገባ መረዳት ጀምሯል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የቀድሞው የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ቲቦር ናዥ ይህንን የግብጽን ጨፍኑ ላሞኛችሁ አካሄድ ሰሞኑን በጥልቅ አመክንዮአዊ መልዕክት አጋልጠውታል።

አምባሳደሩ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ "ግብጽ እና ኤርትራ በቀይ ባሕር ላይ መወሰን ያለባቸው ተዋሳኝ ሀገራት ብቻ ናቸው ካሉ፤ እንግዲያውስ በአመክንዮ ደረጃ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይም መወሰን ያለባቸው ውኃውን የሚያመነጩት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ብቻ ናቸው" በማለት የካይሮን ክርክር መሠረተ ቢስነት በአደባባይ አሳይተዋል።

አምባሳደሩ ከዚህ ቀደምም ግብጽ ጊዜ ያለፈበትን አካሄድ ትታ መሬት ላይ ወዳለው እውነታ መምጣት እንዳለባት በተደጋጋሚ አሳስበዋል። ኢትዮጵያን በዛቻ እና በግፊት ማንበርከክ እንደማይቻል የገለጹት አንጋፋው ዲፕሎማት፣ የቀይ ባሕር ደኅንነት ያለ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ ሙሉ ሊሆን እንደማይችል በግልጽ አስምረውበታል።

ግብጽ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ስትገነባ "የታችኛው ተፋሰስ ፈቃድ ያስፈልጋል" እያለች አቤቱታ ስታሰማ፣ በሌላ በኩል ደግሞ .. 2020 በሪያድ የተቋቋመውን "የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ሀገራት ምክር ቤት" በመጠቀም ኢትዮጵያን ከባሕር ደኅንነት ውይይቶች ለማግለል ስትሠራ ቆይታለች።

ይህ "ራሴን በጉያዬ፣ የሌላውን በጋራ" የብልጠት ስትራቴጂ አሁን ላይ ጊዜው አልፎበታል። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የልማት ጥያቄዋን በአግባቡ መጠየቅ እና በውኃዋም ሆነ በባሕር በር አማራጮቿ ተጠቃሚ ለመሆን መንቀሳቀስ በመጀመሯ፣ የግብጽ ያረጀ የሞኖፖል እና የሴራ አካሄድ ፈጽሞ እንደማያዋጣ በተግባር እየተረጋገጠ መጥቷል።

ለግብጽ የሚበጃት ብቸኛ መንገድ ወደ እውነታው መምጣት እና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሐዊ የትብብር ማዕቀፍን መቀበል ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን ሕዝቧን የልማት እና የደኅንነት ዋስትና ለማረጋገጥ የጀመረችውን የሰላም እና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዞ ማንም አያስቆመውም።

በለሚ ታደሰ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: