Search

የመደመር መንግሥት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው - የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር

ሰኞ ሐምሌ 20, 2018 30

የመደመር መንግሥት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ያብራሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር 2018 በጀት ዓመት የአካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ አፈፃፀም እና 2019 ዕቅድ ላይ ከክልሎች እና ከከተማ መስተዳድሮች ጋር ባካሄዱት የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የከፋ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ቅድሚያ መስጠት ዋነኛው እና ቀዳሚው መፍትሔ መሆኑ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ የካርቦን ልቀት የምታበረክተው አስተዋፅኦ አነስተኛ ቢሆንም፣ ከችግሩ ከፍተኛ ተጋላጭ ሀገራት መካከል እንደምትገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ሀገራችን የችግሩ ሰለባ ብቻ ሳትሆን ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ የመፍትሔው አካል ለመሆን በግንባር ቀደምትነት እየሠራች መሆኑንም አስረድተዋል።

በውይይቱ ወቅት እንደተገለጸው፣ የታዳሽ ኃይል ልማትን ማስፋፋት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አቅም ማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የግብርና ሥርዓትን ማጠናከር እና የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እንደ ዋና መሣሪያ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በጥቂት ዓመታት ውስጥ 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አቶ ስዩም አንስተዋል።

ይህም የሀገራችንን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ከመጨመሩ ባሻገር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ዕውቅናና አድናቆት ያተረፈ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 2ኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት ማስተናገዷ እና 32ኛውን የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) እንድታዘጋጅ መመረጧ ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ለተገኘው ውጤታማ ሥራ የተሰጠ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ማረጋገጫ እንደሆነ ገልጸዋል።

በባዬ ሙላት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: