Search

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባሻገር በኢኮኖሚው ዘርፍ አበረታች ውጤቶችን እያመጣ ነው - ዓለምፀሐይ ጳውሎስ

ሰኞ ሐምሌ 20, 2018 27

የጠቅላይ ሚኒስትር /ቤት፣ የቤተ መንግሥት አስተዳደር እና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

በቆቃ ቤተ መንግሥት ይዞታ ሥር በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የምግብ ዋስትናን ከሚያረጋግጡ የፍራፍሬ ተክሎች ጋር የተለያዩ ዘሮች ተተክለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትር /ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሀይ ጳውሎስ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በርካታ ሁለንተናዊ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል አቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ አያይዘውም መርሐ ግብሩ ለአየር ንብረት ጥበቃ ካለው ፋይዳ ባለፈ በመርሀ ግብሩ አማካኝነት የተተከሉ እንደ ቡና እና አቮካዶ ያሉ ችግኞች ምርት በመስጠት የዜጎችን ኢኮኖሚ እያሳደጉት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በቆቃ ቤተ መንግሥት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ከፍተኛ የፍራፍሬ ምርት እየተገኘ እንደሚገኝ የገለጹት ሃላፊዋ በዘንድሮው መርሃ ግብርም አቮካዶን ጨምሮ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ሌሎች ችግኞች እየተተከሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ከሚጫወተው ታላቅ ሚና በተጨማሪ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

በአባዲ ወይናይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: