የ2026 የአፍሪካ ሎጂስቲክስ እና ኮሙዩኒኬሽን ሲምፖዚየም በይፋ ተከፍቷል።
ዝግጅቱን በይፋ ከፍተው ንግግር ያቀረቡት የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ፣ አዲስ አበባን የሲምፖዚየሙ አስተናጋጅ ከተማ አድርጎ ለመምረጥ የተወሰነው ውሳኔ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል እያደገ የመጣውን የጋራ መተማመን እና የስትራቴጂክ አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በዲፕሎማሲ እና በወታደራዊ ትብብር ዘርፍ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ደረጃ መሸጋገሩን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በኢትዮጵያ ላይ ለተጣለው እምነት እና አመኔታ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሲምፖዚየሙ ከቴክኒካዊ ውይይቶች ባሻገር አጋርነትን የሚያጠናክር፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን የሚያጋራ እና በመላው አፍሪካ ብቁ፣ የተሣሠሩ እና ለወደፊቱ ዝግጁ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት የጋራ ቁርጠኝነትን የሚያጠናክር መድረክ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
እንዲሁም በትብብር እና በፈጠራ አማካኝነት የዝግጁነት አቅምን ማሳደግ፣ በአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ኃይሎች መካከል የተቀናጀ አሠራርን ማጠናከር እና ለአህጉሪቱ ሰላም፣ ደኅንነት እና ዘላቂ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የበለጠ ማጎልበት የሲምፖዚየሙ ዋና ዓላማ መሆኑን መግለጻቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በዝግጅቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ (አፍሪኮም) ጄኔራል ዳግላስ አንደርሰን፣ የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራማን እስማኤልን ጨምሮ ከአርባ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮች እና 26 ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪ ተወካዮች ተገኝተዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: