Search

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለኢትዮጵያ ተጨማሪ 468 ሚሊዮን ዶላር ለመልቀቅ በሠራተኞች ደረጃ ስምምነት ላይ ደረሰ

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 52

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የልዑካን ቡድን እና የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ 468 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለመልቀቅ የሚያስችስ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በሠራተኞች ደረጃ (Staff-Level Agreement) የተደረሰው ይህ ስምምነት በሚቀጥሉት ሳምንታት በድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ሲጸድቅ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።

ይህም ኢትዮጵያ እስካሁን ከተቋሙ ያገኘችውን አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ ወደ 2.65 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል።

ይህ ስምምነት የተደረሰው ተቋሙ ለኢትዮጵያ በፈቀደው 4 ዓመት 3.4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) አምስተኛውን ክለሳ ተከትሎ ነው።

በአልቫሮ ፒሪስ የተመራው እና ውይይቱን በበይነመረብ የቀጠለው የልዑካን ቡድን ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዋን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ተስፋ ሰጪ የማክሮ ኢኮኖሚ ውጤቶች እያሳየች መሆኑን ገልጿል።

በዚህም መሠረት እስከ ፈረንጆቹ 2026 መጀመሪያ ድረስ የወጪ ንግድ፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እና የመንግሥት ገቢ መሻሻል ማሳየታቸውን እና የዋጋ ግሽበትም መቀነሱን ጠቁሟል።

በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ እክል መፍጠሩ እና የነዳጅ እና ማዳበሪያ ዋጋ እንዲንር ማድረጉ በውጫዊ ጫናነት ቢጠቀስም፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁንም ጠንካራ እንቅስቃሴ እያሳየ እንደሚገኝ እና ያደረሰው ተጽዕኖ መጠነኛ መሆኑን የልዑካን ቡድኑ አረጋግጧል።

ይሁን እንጂ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን በዘላቂነት ለማስቀጠል እና በግል ዘርፍ የሚመራ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን መከተል፣ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ግልጽነትን ማሻሻል፣ የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ እና የቢዝነስ ከባቢን ማሻሻል እንደሚገባ ድርጅቱ አሳስቧል።

በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያን የዕዳ ቅነሳ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከይፋዊ አበዳሪዎች እና ከዩሮቦንድ ባለቤቶች ጋር እየተደረገ ያለው የዕዳ ሽግሽግ ውይይት መልካም ዕድገት እያሳየ መሆኑ ተገልጿል።

የልዑካን ቡድኑ በአዲስ አበባ በነበረው ቆይታ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ፣ ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (/) እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከግል ዘርፍ እና ከልማት አጋሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጉን በነዚሁ መግለጫው አስታውቋል።

 በለሚ ታደሰ