በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አምራችና ሸማቾችን በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ታሳቢ ተደርጎ የተገነባው ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የገበያ ማዕከሉን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፤ መንግሥት የኑሮ ውድነትን እንደ አንድ ቁልፍ የኢኮኖሚ ችግር መለየቱን ጠቁመው፣ ችግሩን ለመከላከልም የገበያ ማዕከላትን መገንባትን ጨምሮ የተለያዩ ሰው ተኮር ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ይህ ማዕከል የፋብሪካና የግብርና ምርቶች በቀጥታ ቀርበው አምራችና ሸማች የሚገበያዩበት ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም የክልሉ መንግሥት የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦቶችን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የረጅም የግብይት ሰንሰለትን በመቁረጥ የደላላ ጣልቃ ገብነትን ለማስወገድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማውም፣ ማዕከሉ ለአካባቢው ማህበረሰብ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ምቹ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ይህ ስራ በክልሉ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋትና የሸማቹን ህዝብ የመግዛት አቅም ለመጠበቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በምርቃቱ ወቅት ተመላክቷል።
በተስፋሁን ደስታ